በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዶሎ ዞን ላይ ያወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ በትክክል የማያንጸባርቅና በችኮላ የወጣ ነው ሲል የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው መስከረም 7 ቀን 2019 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ በሰጠው አስቸኳይ መግለጫ፣ ማስጠንቀቂያው በየጊዜው ሁኔታዎችን ከሚከታተሉት የክልሉ አስተዳደርና የፀጥታ ተቋማት ጋር በቂ የመረጃ ማጣራትና ምክክር ሳይደረግበት የወጣ መሆኑን ገልጿል።
እንደ ክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት የዶሎ ዞን ሙሉ በሙሉ ሰላማዊና የተረጋጋ ነው። በዞኑ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት መደበኛ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ሲሆን፤ የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ፣ የንግድ ሥራዎች፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲሁም ሌሎች ዕለታዊ ተግባራት ያለምንም የእንቅስቃሴ ገደብ በመደበኛ ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
የክልሉ አስተዳደር ለነዋሪዎች፣ ለእንግዶችና ለዜጎች ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ የጠቆመው መግለጫው፤ ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ የፀጥታ ሁኔታ ካጋጠመ የሚመለከታቸው አካላት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝቡ እንደሚያደርሱ አስታውቋል።
በመሆኑም የዲፕሎማሲ ተቋማት መሰል ማስጠንቀቂያዎችን ከማውጣታቸው በፊት መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመመካከር እንዲያጣሩና አላስፈላጊ ሥጋት ከመፍጠር እንዲቆጠቡ ጥሪ ቀርቧል።
#FastMereja
