#FastMereja I ግብፅ ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የምታካሂደው “አንድ ወገን ውሳኔ እና እንቅስቃሴ” ተቀባይነት የለውም ስትል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላለፈች። የሃገሪቱ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀኒ ሴዊላም በካይሮ ለተሰበሰቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ግብፅ የውሃ ደህንነቷን ለማስጠበቅ በአለም አቀፍ ህግ የተፈቀዱትን ማንኛውንም አይነት እርምጃዎች የመውሰድ መብቷ የተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ግብፅ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን በግንባታ፣ በውሃ ሙሌት እና በእንቅስቃሴ ሂደት የተከተለችውን አካሄድ “ህገ-ወጥ” እንደሆነ አድርጋ የምትቆጥረው ሲሆን፣ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅም ሆነ ጊዜ ማለፉ የካይሮን ይሁኝታ አያሳይም ብለዋል። አሁንም ቢሆን የህዳሴው ግድብ ህገ-ወጥ እንደሆነ ይቀጥላል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ግብፅ በናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚከናወኑ የልማትና የግድብ ግንባታዎችን እንደማትቃወም የጠቆሙት ሴዊላም፤ ተቃውሟቸው በጋራ የውሃ ሀብት ላይ የሚደረጉ አደገኛ እና አንድ ወገን ብቻ ያላቸውን ውሳኔዎች ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በተቀናጀ መንገድ የማይመራው የህዳሴው ግድብ የውሃ ፍሰት ወደ ግብፅ እና ሱዳን በሚሄደው የውሃ መጠን ላይ ድንገተኛ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችልና ይህም በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በሚገኙ ሌሎች ግድቦች ላይ አደጋ እንደሚፈጥር አሳስበዋል። ይህ ሂደት “ሰው ሰራሽ የጎርፍ አደጋ” ወይም “ሰው ሰራሽ ድርቅ” ሊያስከትል እንደሚችል በመጠቆም፣ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን የህይወትና የሞት ጥቅም አሳልፋ አትሰጥም ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስትሩ ካይሮ በተፋሰሱ ሀገራት የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን እንደምትደግፍ ገልጸው፤ በደቡባዊ ናይል ተፋሰስ ለሚተገበሩ 36 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ መስማማቷን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል በደቡብ ሱዳን የሚገነባውን የግራንድ ፉላ ግድብ ፕሮጀክት በምሳሌነት አንስተዋል። ግብፅ እስካሁን ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶችን በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት መተግበሯን እና ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር በጅምር ካፒታል የተመደበለት አዲስ የልማት ፈንድ ማቋቋሟን ይፋ አድርገዋል።
ከሀገራቸው የውሃ እጥረት ጋር ተያይዞም ሚኒስትሩ፤ የግብፅ 98 በመቶ የሚሆነው ታዳሽ የውሃ ሀብት ከሀገር ውጭ የሚመጣ መሆኑን ገልጸው፣ የነፍስ ወከፍ የውሃ አቅርቦት በዓመት ወደ 472 ኪዩቢክ ሜትር ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል። ይህም ከአለም አቀፍ የውሃ እጥረት መስፈርት በታች በመሆኑ ሀገሪቱ የባህር ውሃ ማጣራትና ቆሻሻ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን ብትጀምርም፣ የባህር ውሃ ማጣራት ግን የናይል ወንዝን ሊተካ እንደማይችልና አሁንም ናይል ዋነኛ የህይወት ምንጫቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ምንጭ የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ።
