banner

የወተት ጥራትና ደህንነት ዋነኛ መነሻ ከከብቶች መኖ አያያዝ እንደሚጀምር ተገለጸ!

#Fastmereja:- ለህብረተሰቡ የምግብ ገበታ የሚቀርበው የወተት ምርት ጥራትና ደህንነት ዋነኛ መነሻ ከከብቶች መኖና ከእንስሳቱ አያያዝ እንደሚጀምር ባለሙያዎችና የዘርፉ ተቆጣጣሪ አካላት አስታወቁ።

ወተትን ከእርሻ እስከ ተጠቃሚው ጭልፋ በሚደርስበት ረጅም መንገድ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ምርት ሲሆን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) ባወጣው መረጃ መሰረት፣ በወተት እሴት ሰንሰለት (Value Chain) ውስጥ የመጀመሪያው እና ወሳኙ ደረጃ የከብቶች መኖና ንፅህና መሆኑ ተገልጿል።

አርሶ አደሮችና አርቢዎች ለላሞች የሚሰጡት መኖ ከሻጋታ፣ ከመርዛማ ኬሚካሎችና ከባክቴሪያ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይም በእርጥበት ምክንያት በሚከሰት የሻጋታ መኖ ውስጥ የሚፈጠረው አፍላቶክሲን (Aflatoxin) የሚባል አደገኛ መርዝ በቀጥታ ወደ ወተት በመሸጋገር በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያስከትል ተመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ የወተቱ የቅባት፣ የፕሮቲን እና የቪታሚን ይዘት እንዲሁም ተፈጥሯዊ ጣዕሙ ሙሉ በሙሉ የሚወሰነው ላሞች በሚመገቡት መኖ ጥራት ላይ መሆኑ ተጠቅሷል።

በመሆኑም አርቢዎች መኖን በደረቅና አየር በሚዘዋወርበት ቦታ በማከማቸት ከሻጋታ እንዲጠብቁ፣ ንጹህ ውሃ እንዲያቀርቡ እና የእንስሳቱን መጠለያ ንፅህና መደበኛ ክትትል እንዲያደርጉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ አጓጓዦች፣ ማቀነባበሪያዎችና ነጋዴዎችም በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን የማቀዝቀዝ እና የንፅህና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተሳስቧል።

ህብረተሰቡ ጥራትና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ የወተት ምርት ሲያጋጥመው ወደ 8482 በነፃ በመደወል ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ባለሥልጣኑ አስታውቋል።








Leave a Comment