banner

በሀገሪቱ ያጋጠመውን የኮንዶም እጥረት ለመቅረፍ ለ18 ወራት የሚሆን በቂ አቅርቦት ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ተገለጸ

#FastMereja I ዲኬቲ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ያጋጠመውን የስነ-ተዋልዶ ጤና ግብአቶች እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል ለ18 ወራት የሚሆን በቂ የኮንዶም አቅርቦት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን አስታወቀ። ተቋሙ በ2026 ለማሰራጨት ካቀደው እስከ 40 ሚሊዮን የሚደርስ መጠን ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉ ተገልጿል።

​የዓለም አቀፍ የእርዳታ አቅርቦቶች በመቀነሳቸው ያጋጠመውን እጥረት ለመፍታት ተቋሙ በግዥ፣ በሎጅስቲክስ እና በስርዓት ዝርጋታ ሰፊ የሪፎርም ስራ መሰራቱን የኦፕሬሽን ክፍል ሀላፊ አቶ አሳይየ ደምሴ ገልጸዋል። በተጨማሪም የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የአለም ጤና ድርጅት መስፈርቶችን ያሟላ ዘመናዊ ማዕከላዊ መጋዘን በመገንባትና በማስመረቅ የመድኃኒቶችና የኮንዶም ጥራት ሳይበላሽ እንዲጠበቅ መደረጉ ተብራርቷል።

​ይህ አቅርቦት በሶሻል ማርኬቲንግ አሰራር ድጎማ በማድረግ ለግል ጤና ተቋማት፣ ለፋርማሲዎች፣ ለኪዮስኮች፣ ለቡፌዎችና ለሆቴሎች በተመጣጣኝ ዋጋ የማዳረስ ስራ እየተሰራ ይገኛል። እንዲሁም በ7 የክልል ማዕከላት በኩል ጥያቄ በቀረበ በ24 ሰዓት ውስጥ አቅርቦት የሚያደርስ ፈጣን አሰራር እና የደንበኞች የአጭር ስልክ ጥሪ ማዕከል መዘርጋቱ ተነግሯል።

​ዘገባው የኢትዮ ኤፍ ኤም ነው።









Leave a Comment