#FastMereja I ቪዛ (Visa) ከተባለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ እና ከኢታ ሶሉሽንስ (ETTA Solutions) ጋር በመተባበር በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ 148 ሺህ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ትላልቅ ነጋዴዎችን የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የአጋርነት ስምምነት ይፋ አደረጉ። ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደ ተነገረው፣ ይህ ጥረት በሀገሪቱ ያለውን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እና የፋይናንስ ተደራሽነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው።
በዚህ መርሃ ግብር መሠረት 148 ሺህ የዞሪያ (Zoorya) ክፍያ መቀበያ መሳሪያዎች እና ዘመናዊ የPOS ተርሚናሎች ለነጋዴዎች የሚሰራጩ ሲሆን፣ ይህም ነጋዴዎች በተለያየ መንገድ ክፍያ እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል። በካርድ (Contactless)፣ በQR ኮድ፣ በሞባይል ገንዘብ እንዲሁም ከሂሳብ ወደ ሂሳብ የሚደረጉ ክፍያዎችን በአንድ መሳሪያ ላይ ማስተናገድ የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም መሳሪያዎቹ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ መስጠት፣ የሽያጭና የክምችት ቁጥጥር እንዲሁም አጠቃላይ የንግድ አስተዳደርን የሚያቀሉ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ያካተቱ ናቸው።
ከክፍያ መቀበያ አገልግሎቱ ጎን ለጎን ነጋዴዎች የሥራ ማስኬጃ ብድር የሚያገኙበት አዲስ አሠራር መዘረጋቱ ተገልጻል። አጋርነቱ ከኦፕታሲያ (Optasia) እና ከተለያዩ አጋር ባንኮች ጋር በመተባበር ነጋዴዎች የሚያካሂዱትን የግብይት ታሪክ መሠረት በማድረግ በቀላሉ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ያመቻቻል።
የፕሮግራሙ አፈጻጸም በመጀመሪያ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ደረጃ በደረጃ ወደ መላው የሀገሪቱ ክልሎች የሚስፋፋ ይሆናል።




