banner

ዘምዘም ባንክ እና አሚዮ ኢንጂነሪንግ በሙሻራካ ፋይናንስ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ስትራቴጂያዊ አጋርነት መሠረቱ

#FastMereja I ዘምዘም ባንክ አ.ማ. እና አሚዮ ኢንጂነሪንግ የግብርና ትራክተሮችን ገዝቶ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል፣ በኢስላሚክ ፋይናንስ «ሙሻራካ» መርህ ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂያዊ የትብብር ስምምነት ይፋ አደረጉ። አጋርነቱ “በአጋርነት የግብርና ሽግግርን ማስፋፋት” በሚል መሪ ቃል በተካሄደ ይፋዊ የማስጀመሪያና የማሰያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ የሸሪዓን መርሆች የጠበቀ አሠራር ምርታማ ኢንቨስትመንትን እንዴት መደገፍ እንደሚችል በተግባር ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ የፋይናንስ አጋርነት አማካይነት የኢስላሚክ ፋይናንስ አሠራር ከግብርና ቴክኖሎጂ ጋር በመቀናጀቱ፣ ደንበኞችና አርሶ አደሮች ለምርታማነታቸው አስፈላጊ የሆኑ የግብርና መሣሪያዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችላቸው ዕድል ተፈጥሯል። ይህም የሙሻራካ ፋይናንስ ሞዴል በእውነተኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ቀጥተኛና ምርታማ የሆነ ኢንቨስትመንት ላይ መዋሉን የሚያረጋግጥ እርምጃ መሆኑን ከተቋማቱ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።

የትብብር ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከኦሮሚያ ክልል ግብርና ዘርፍ፣ ከትራክተር አምራች ድርጅቶች እንዲሁም ከፋይናንሱ ተጠቃሚ ደንበኞች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል። ይህ የመንግሥትና የልማት ተቋማት ተሳትፎ በፋይናንስ ተቋማት፣ በቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና በአርሶ አደሩ መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር ትልቅ መድረክ መፍጠሩ ተመላክቷል።

ዘምዘም ባንክ በበኩሉ ከተለመዱት የባንክ አገልግሎቶች ባሻገር የሸሪዓን መርሆች የጠበቁ የፋይናንስ መፍትሔዎችን በማቅረብ ዘላቂ የግብርና ዕድገትን ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል። ይህ አጋርነት በቀጣይም በፋይናንስ ተቋማትና በግብርና መሣሪያዎች አቅራቢዎች መካከል የሚደረጉ መሰል ትብብሮችን በማስፋፋት ለሀገሪቱ የግብርና ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።





Leave a Comment