banner

በአዲስ አበባ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች ከገበያ ተወገዱ፤ 33 ያልተፈቀደላቸው አምራቾች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ባለፉት ሦስት ወራት በ1,561 የንግድ ድርጅቶች ላይ ባካሄደው የገበያ ቅኝትና ክትትል፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ሸማቾችን የሚጎዱ የተለያዩ ምግብ ነክና የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ከገበያ እንዲወገዱ ማድረጉን ገለጸ። በቢሮው የሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ደበሌ እንዳስታወቁት፤ የቅኝት ሥራው በየደረጃው በሚገኘው የሸማቾች መብት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የተካሄደ ሲሆን፣ በገበያ ላይ የሚቀርቡ ምርቶች የጥራት ደረጃቸውንና የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

በክትትሉ ከገበያ እንዲወገዱ ከተደረጉት ምርቶች መካከል የታሸጉ የለስላሳ መጠጦች፣ የሕጻናት ምግቦች፣ ብስኩቶች፣ ኢንዶሚ፣ የልብስ ማጠቢያና የእጅ ሳሙናዎች፣ ሻምፖዎች፣ ሎሽኖች፣ የፀጉር ቅባቶች፣ የምግብ ዘይት፣ የለውዝ ቅቤ፣ የገበታ ጨው፣ ሻይ ቅጠል፣ ጁስ፣ ካቻፕ፣ ቸኮሌት፣ ከረሜላ እና ማስቲካ ይገኙበታል።

በተጨማሪም ቢሮው በ62 አምራች ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር ያደረገ ሲሆን፣ የማምረት ፈቃድና የምርት ጥራት ሰርተፍኬት ሳይኖራቸው ምርት ሲያመርቱ በተገኙ 33 የለውዝ ቅቤ አምራቾች ላይ በወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል የምርት ጥራታቸው አጠራጣሪ የሆኑ 20 ምርቶች ናሙና ተወስዶ በተደረገ ምርመራ የጥራት ደረጃቸውን ያላሟሉ ሰባት ምርቶች (ሦስት ፈሳሽ የልብስ ሳሙናዎች፣ ሦስት የለውዝ ቅቤዎች እና አንድ አዮዳይዝድ የምግብ ጨው) ተለይተዋል። ከተለዩት መካከል ሦስቱ በኦሮሚያ ክልል፣ አንዱ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ በመሆናቸው በየክልሎቹ በኩል ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ኃላፊው አብራርተዋል።

አቶ ጸጋዬ አያይዘውም የጥራትና የመጠቀሚያ ጊዜ ቁጥጥር ሥራው ሸማቾችን ከጤናና ከኢኮኖሚያዊ ኪሳራ የመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ ህብረተሰቡ የጥራት ጉድለት ወይም አጠራጣሪ ምርቶችን ሲመለከት በቢሮው ነፃ የስልክ መስመር 8588 ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።

Leave a Comment