#Fastmereja:-15ኛው የኢትዮ ዶሮ ኤክስፖ (ኢትዮፔክስ) እና 11ኛው የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት አውደ ርዕይና ጉባኤ (አሌክ)ን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ዛሬ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር (AICC) በይፋ ተከፈቱ።
ከዛሬ ጥቅምት 19 እስከ 21 ቀን 2019 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ይህ ታላቅ ኩነት፤ 14 ሀገራትን የሚወክሉ ከ130 በላይ ተሳታፊ ድርጅቶችን ያሰባሰበ ሲሆን፣ ከ4,000 በላይ የንግድ ጎብኚዎችና ባለሀብቶች ይገበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፕራና ኤቨንትስ ከኤክስፖ ቲም ፎር ሰርቪስ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ መድረክ፤ የኢትዮ ዶሮ ኤክስፖ፣ የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት አውደ ርዕይ፣ 6ኛው የኢትዮጵያ የማር ኤክስፖ፣ የኢትዮጵያ የአሳ ኤክስፖ እንዲሁም የባዮ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ጣሪያ ስር አያይዞ አቅርቧል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ በእንስሳት ሀብት እሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችን፣ ባለሙያዎችንና የልማት አጋሮችን በማገናኘት የንግድ ትስስርን፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ልውውጥን ማጠናከር መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዝግጅት የኔዘርላንድስ ኤምባሲ በብሔራዊ ፓቪሊዮን የተሳተፈ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ኩባንያዎች በመኖ እና የወተት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያሏቸውን መፍትሔዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በ2018 የበጀት ዓመት በአገሪቱ ከ15.8 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት እና 11.7 ቢሊዮን እንቁላል የተመረተ ሲሆን፣ የዚህ ዓይነቱ አውደ ርዕይ የ”ሌማት ትሩፋት” መርሃ ግብርን በመደገፍ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል።
ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን የዘርፉ ጉባኤዎች፣ የቢዝነስ ለቢዝነስ (B2B) የንግድ ትስስር ውይይቶች እና የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮች በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚካሄዱ ተገልጻል።




