የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “በዓለ ሃምሳ”ን እንደ ሌሎቹ ዓበይት በዓላት በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በድምቀት እንዲከበር ወሰነች
#FastMereja I የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበትን ታላቅ በዓል “በዓለ ሃምሳ” (በዓለ ጰራቅሊጦስ) ከዚህ ቀደም ከነበረው አከባበር በተለየ መልኩ፣ እንደ ዓበይት በዓላት በሁሉም የሀገራችን ክፍሎችና በመላው ዓለም በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በድምቀት እንዲከበር መወሰኑን ቤተ ክርስቲያኗ አስታወቀች።
እንደ ቤተ ክርስቲያኗ መግለጫ ከሆነ፣ የበዓለ ሃምሳ ታሪክ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ከወረደበት ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ ያለማቋረጥ ሲከበር የኖረ ታላቅ መንፈሳዊ ምዕራፍ ነው። ይሁን እንጂ በዓሉ ከዚህ ቀደም በሀገራችን ብሔራዊ ደረጃ ከሚሰጣቸው ሌሎች ዓበይት በዓላት ማለትም ከበዓለ ልደትና ከበዓለ ትንሣኤ ጋር ሲነፃፀር ሲሰጠው የነበረው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ይታወሳል።
ይህን ክፍተት በመሙላት የበዓሉን መንፈሳዊና ታሪካዊ ፋይዳ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በሚገኙ አህጉረ ስብከት ሁሉ በድምቀትና በታላቅ ዝግጅት እንዲከበር ውሳኔ ላይ መደረጉ ተገልጿል። ይህ ውሳኔ ምዕመናን የበዓሉን ጥልቅ ትርጉም በጋራ እንዲለማመዱና የቤተ ክርስቲያኗን አንድነትና ህብረት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ትልቅ እርምጃ መሆኑ ታምኖበታል።
