#Fastmereja:-የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት (EQA) 13ኛውን ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሥነ ሥርዓት ኅዳር 12 ቀን 2019 ዓ.ም. ከምሽቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በታላቁ ቤተ መንግሥት ጉባኤ አዳራሽ እንደሚያካሂድ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት እንዳስታወቁት፤ በዘንድሮው ውድድር በአምራች፣ በአገልግሎት፣ በጤና፣ በመንግሥት አገልግሎት እና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የተመዘገቡ 71 ተቋማት የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም 32 ነባር፣ 23 አዲስ እና 3 ከዚህ ቀደም ያለፉ በድምሩ 58 ድርጅቶች የምዘና ሂደቱን በስኬት ያጠናቀቁ መሆናቸዉን ገልፀዋል።
የዘንድሮው ውድድር ለአራተኛ ጊዜ በጥልቀት በተከለሰ የማወዳደሪያ መስፈርትና የራስ ምዘና ማንዋል መመራቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ክለሳውም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂን፣ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030»ን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እንዲሁም የ2025 ዓለም አቀፍ የልህቀት ሞዴሎችን (Malcolm Baldrige እና EFQM) ባካተተ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ክቡር አቶ ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታላላቅ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የንግድ ማኅበረሰቡ ተወካዮች፣ የጥራት ባለሙያዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሚታደሙበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የአሸናፊ ድርጅቶች ስም ዝርዝርና የሽልማት ደረጃ በይፋ እንደሚገለፅም ነዉ የተብራራዉ።
ከ19 ዓመታት በፊት በ2000 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት (EQA) በአገሪቱ የጥራት ግንዛቤን ለማሳደግና በምርትና አገልግሎት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማትን ለማበረታታት በየዓመቱ ብሔራዊ የጥራት ሽልማት መርሐ ግብሮችን እንደሚያከናውን ይታወቃል።




