banner

በጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት ናዳ የሟቾች ቁጥር 157 ደረሰ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ ትላንት ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም ረፋድ አካባቢ የተከሰተው የመሬት ናዳ እስካሁን ባለው መረጃ ከ157 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

የጎፋ ዞን አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለፁት በመሬት ናዳው በአንድ የቤተሰብ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ እነሱን ለማትረፍ እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለነብስ አድን ሥራ ወደ ስፍራው ባቀኑ ሰዎች ላይ ተጨማሪ አደጋ በመድረሱ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ችሏል።

በአደጋው ለነብስ አድን ሥራ ቀድመው በስፍራው የተገኙ የቀበሌውን አስተዳዳሪ ጨምሮ መምህራን፣ የጤና ባለሞያዎች እና የግብርና ባለሞያወች የአደጋው ሰለባ ሆነዋል።

በዞኑ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ አደጋ ያጋጥም የነበር በመሆኑ ነዋሪዎችን የአደጋ ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች የማሸሽ ስራ ቢሰራም ተመሳሳይ አደጋ ይደርስበታል ተብሎ ባልታሰበ ሌላ ቀበሌ አደጋው ማጋጠሙ ሁኔታውን ይበልጥ አሳዛኝ አድርጎታል ብለዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ በአሁኑ ሰአት የተጎዱ ሰዎችን ነብስ ለማዳን እና ለተጎጂዎች የመጠለያ እና ምግብ በማቅረብ በርብርብ ላይ ይገኛል ሲሉ አቶ ዳግማዊ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ እና ከአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች የተወጣጡ ባለሞያዎች በሥፍራው በመገኘት ለተጎጂዎች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

እስካሁን 5 ሰዎች ከናዳው ውስጥ በሕይወት መውጣት መቻላቸውን እና በሕህክምና ተቋማት የጤና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም የዞኑ አስተዳዳሪ ጠቁመዋል።

በስፍራው የነብስ አድን ስራ እየተከናወነ የሚገኘው በሰው ኃይል ብቻ መሆኑን የጠቆሙት የዞኑ አስተዳዳሪ ለተጨማሪ የነብስ አድን ስራ የሚያስፈልጉ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ እና ትኩረት ወደ ዞኑ እንዲሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Comment