banner

“ሀገርን ለማስቀጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል!” – ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተሰጠው ስልጣን እና ተግባር መሰረት ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል ። ይሁን እንጂ በተቋሙ አሰራር የሚረካ እንዳለ ሁሉ ደስተኛ ያልሆነ ወይም ቅሬታ ያለው አካል ሊኖር ይችላል። ይህ በየትኛውም ድርጅት ያለና የሚኖር ነው።

ተቋሙ በስፖርት መድረክ አለመግባባቶች እና ቅራኔዎች ሲኖሩ የሚስተናገዱበት መንገድ በመተዳደሪያ ደንቡ በግልፅ አስቀምጧል። አንቀፅ 38 ላይ ” በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ወይም በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና በአባላቱ መካከል የሚነሱ ማናቸውም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ወይም ተቋማዊ ቅራኔዎች በሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የአስተዳደር አባላት ( በሜኔጅመንት በቦርድ ወይም በጠቅላላ ጉባኤ ወይም ለዚሁ ችግር አፈታት በሚቋቋም የፍትህ አካል ይፈታል ።

[ ከስፖርት ጋር የተያያዙ ያለመግባባቶችና ቅሬታዎች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ውጭ ይፈታሉ ።]

ጉዳዩ ለስራ አስፈፃሚ ቦርድ እና / ወይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ የስልጣን አካል ለሆነው ለጠቅላላ ጉባኤው ይመራል። ጠቅላላ ጉባኤው በቀረበው ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ወይም ቅራኔውን ለመፍታት የእርቅ ፣ የግልግል ወይም የሽምግልና አካል እንዲሰየም ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል ።

በቀረበው ቅራኔ ላይ የተሰጠ ማንኛውም የመጨረሻ ውሳኔ በአቤቱታ መልክ ብቻ ሉዛን ስዊዘርላንድ ለሚገኘው የስፖርት ዳኝነት ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይችላል ።

አቤቱታውን ማቅረብ የሚቻለው የሚመለከተው ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በ21 ቀናት ቀነ ገደብ ውስጥ ነው። ” ይላል ።

በዚህ መሰረት :-

1ኛ / የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ እና መደበኛ ፍርድ ቤት ስልጣን እንደሌላቸው እየታወቀ ህግና ስርአትን ተከትሎ ጥያቄ ማንሳት ሲገባ የውሸት ቃለ መሀላ በማቅረብ እና ተረኛ ችሎቱን በማሳሳት እግድ ያወጡበት መንገድ ከሳሽ ነን የሚሉት ግለሰቦች ተከራክረው ማሸነፍ የሚችሉበት የእውነተኛ የሕግ መሰረት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል።

በተጨማሪም በውሸት ቃለ መሀላ ያገኙትን እግድ ልክ ተከራክረው እንዳሸነፉ መግለጫ መስጠታቸው የቱን ያህል በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት እንደማይሰሩ በግልፅ የሚያሳይ ነው።

ሀገርን ለማስቀጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።

2ኛ/ በአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) ሙሉ በሙሉ የታገደው እና እውቅና በግልፅ የተከለከለው እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ያልሆነው በአቶ እያሱ ወሰን የሚመራው የቀድሞው የቦክስ ፌዴሬሽን ከሳሽ ሆኖ መምጣቱ ” እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል! ” እንዳለችው እንስሳ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ይዤ ልውደቅ ከሚል ክፉ መንፈስ የመነጨ በመሆኑ ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘበው ለመግለፅ እንወዳለን።

3ኛ/ ሻለቃ ሀይሌ ገብረሥላሴ የባለፉትን አራት አመታት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝደንት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። ነገር ግን ራሱን ‘ከደሙ ንፁህ ነኝ’ በሚል እና ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በነበረበት ወቅት ለማናጀሮች እና ለስፖርት ትጥቅ አምራች ካምፓኒዎች አሳልፎ በመስጠት ብሄራዊ ቡድን ያፈረሰው ራሱ ሆኖ እያለ የስፖርቱ ተቆርቋሪ ሆኖ መምጣቱ እጅግ አሳዝኖናል።

ለመሆኑ ሻለቃ ሀይሌ ገብረሥላሴ የባለፉትን አመታት የት ነበር ?

4ኛ/ ጀግናው አትሌት ገዛኸኝ አበራ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሆነ ይታወቃል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለበትን የማኔጅመንት ክፍተት ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይዞ መምጣቱ ” ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ! ” የሚባለው ብሂል ዓይነት ነው።

5ኛ/ ከዚህ ቀደም በኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ የስፖርት ትጥቆችን መርካቶ ድረስ ሄደው በመቸብቸብ በፈፀሙት ሕገ ወጥ ተግባር በኮሚቴው የታገዱ አካላት ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ስልጣን በሌለው መደበኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ ሆነው መቅረባቸው እጅግ አሳፋሪ ነው ።

6ኛ/ አንዳንድ የሚዲያ ባለሙያዎች ከግለሰቦች ጋር በግልፅ በገንዘብ በመደለል እና በጥቅም በመተሳሰር (ለዚህም በቂ ማስረጃዎች አሉ ) ለህብረተሰቡ የተዛቡ እና ሚዛናዊ ያልሆኑ የአንድ ወገንን መረጃ ብቻ በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡን እያሳሳቱት ይገኛሉ።

እስካሁን በሆደ ሰፊነት ሁሉንም ችለን አልፈነው የነበረ ቢሆንም ከዚህ በላይ መጓዝ ተቋሙን እና አገርን አደጋ ውስጥ ሊከት ስለሚችል እያንዳንዱን ድርጊታቸውን በማጋለጥ በሕግ የምንጠይቃቸው መሆኑን እንገልፃለን።

[ ከህገ ወጥ ድርጊታቸውም እንዲቆጠቡ ስንል በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።]

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እየተካሄደ ያለውን ግልፅ ሕገወጥ ተግባር የስፖርት ቤተሰቡ ግራ ቀኙን አገናዝቦ እንዲመለከተው ጥሪውን ያስተላልፋል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ታገደ ለሚባለው የደረሰን ነገር ባይኖርም በውሸት ቃለመሀላቸው የተሳሳተ ዳኛ ካለ በሕግ አግባብ እናስቀለብሳለን።

ከሁሉም በላይ እነዚህ ከሳሾች በውሸት ቃለ መሀላ ፍርድ ቤት ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በሕግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እንረዳለን ።

ፈጣሪ አገራችንን ይጠብቅልን !!

በድጋሚ መልካም አዲስ አመት እንመኛለን ።

10 comments

Abdu Rahman September 12, 2024 - 6:03 pm

በድምፅ አንብቡልን ይሄን ሁሉ ማን ያነባል

Reply
Sisay Teshome September 12, 2024 - 6:04 pm

ምክኒያቱ

Reply
የአማራው ፋኖ September 12, 2024 - 6:04 pm

መሬት ላይ ያለው ሀቅ ነው።

Reply
Endesh Girma September 12, 2024 - 6:04 pm

እንዳው ከመስራቤቴ ፍቃድ አግቼ ኦዲት ባደርገው!

እጄ ቢገባ

Reply
Sened Ibrahim September 12, 2024 - 6:05 pm

ትክክል

Reply
ቴድሮስ ኣብ September 12, 2024 - 6:05 pm

የወንዶች ጉዳይ የሚኮራበት ምርጡ አባላችን
የወንጀል ቁና

Reply
Lem Regassa September 12, 2024 - 6:05 pm

ምነው ሀገር ነው እንዴ እሱ?????

Reply
Ones Love September 12, 2024 - 6:05 pm

ጭራሽ እራሱን እንደ ሀገር መቁጠር ጀመረ🤧

Reply
Abichu King September 12, 2024 - 6:06 pm

Ante bicha liqeq lelawu enayalen

Reply
Ethiopics Page Mfw September 12, 2024 - 6:07 pm

አንተ ስለተቀጣ አገር አይቀጣም ተገቢውን ቅጣጥ ማግኘት አልበት።

Reply

Leave a Comment