banner

ራይድ ትራንስፖርት ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ

#FastMereja I ራይድ ትራንስፖርት እና ሰዋሰው መልቲሚዲያ ለሚያስገነቡት ዘመናዊ የራይድ መንደር ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም በገላን ጉራ ከተማ የኦቪድ ግሩፕ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ በመርሃ – ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የአማራጭ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር ኢንጅነር ታምራት አክሊሉ ”በመንግስትና የግል አጋርነት ከሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ከኦቪድ ጋር በትብብር እየሰራን ያለነው አንዱ ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም መንግስት ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ ሌሎች አማሬጮችንም በማቅረብ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

ኦቪድ ሪል እስቴትም እንደ አገር እየገነባቸው የሚገኙ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን አድንቀው፣ ራይድ ትራንስፖርትም ለአሽከርካሪዎቹ ፣ ለተገልጋይ ደንበኞቹ እና በስሩ ላሉ ቤተሰቦች ከኦቪድ ጋር በትብብር ዘመናዊ ከተማን ለመገንባት ያደረገው አጋርነት የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የራይድ ትራንስፖርት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሳምራዊት ፍቅሩ፤ በበኩላቸው ይህንን ፕሮጀክት ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በልባቸው ሲያብሰለስሉት የቆዩ መሆኑን ጠቁመው ፣ አሁን ግን ከኦቪድ ሪል እስቴት ጋር በጋራ ህልማቸው እውን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት በስራቸው የሚገኙ አሽከርካሪዎችን፣ ተገልጋይ ደንበኞቻቸውን እና መላው የራይድ ቤተሰቦችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩም ጭምረው ተናግረዋል፡፡ በኦቪድ ሪል እስቴት በኩልም የፕሮጀክቱን ግንባታ በፍጥነት ወደ ትግበራ በማስገባት ከራይድ ትራንስፖርት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤቶች እንደሚመዘገቡ የኦቪድ ሪልስቴት ግሩፕ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የተገኙ በርካታ የራይድ አሽከርካሪዎችም ኦቪድ ሪል እስቴት እየገነባው ያለውን ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የጎበኙ ሲሆን፤ ስለቤቶቹ ግንባታ ሂደት እና ስለ አጠቃላይ የራይድ መንደር ፕሮጀክት ይዘት፣ የመኖሪያ ቤቶቹን የግንባታ ጥበብ፣ የመኖሪያ መንደሩ ስለሚያካትታቸው ፋሲሊቲዎች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ የራይድ መንደር ግንባታ ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ደንበኞች የሚኖረው ፋይድ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ግንባታውም በፍጥነት እንዲጀመር አሳስበዋል፡፡

በዚህ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ላይ ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ከራይድ ትራንስፖርት፣ ስዋሰው መልቲሚዲያ እና ኦቪድ ሪል እስቴት ዋና ስራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የራይድ አሽከርካሪዎች እና ቤተሰቦች ዝግጅቱን ታድመዋል፡፡





1 comment

Seleshi Begashaw Ayenie November 9, 2024 - 11:11 am

አይ ይቺ አገራችን…….?

Reply

Leave a Comment