በደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ጣቢያ ጋዜጠኛ አብርሃም ሙጎሮ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ያሰባሰባቸውን ከ2 መቶ የሚልቁ መጽሐፍት ለማረሚያ ተቋም አበርክቷል።
የህግ ታራሚዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው መልካም ስብዕና ተጎናጽፈው እንዲወጡ የአዕምሮ ምግብ የሆነውን መጽሐፍትን ማሟላትና ማቅረብ የብዛ-ዕውቀት ባለቤት እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው የሆሳዕና ማረሚያ ተቋም አስታወቀ።
ጋዜጠኛ አብርሃም ለስራ ስምሪት ወደ ሆሳዕና ማረሚያ ተቋም በሄደበት አጋጣሚ በተቋሙ ከፍተኛ የመጻሕፍት ውስንነት መኖሩን በመገንዘብ በግሉ 50 መጽሐፍት ለማበርከት የገባውን ቃል ወደ ማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ፕላት ፎርም በመምጣት መጻሕፍት ማሰባሰብ መጀመሩን ያስታውሳል።
እንደ ባህር ሰፊ ዕውቀት የሚቀዳባቸውን መጽሐፍት ለሰዎች መለገስ፣ እንዲያነቡ ማነሳሳት ልዩ ስሜት እንደሚሰጠው የገለጸው ጋዜጠኛው ጓደኞቹን፣ የስራ ባልደረቦችን፣ ይህን ቀናዕ ሀሳብ የደገፉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማስተባበር ይዘታቸው ላቅ ያሉ 2 መቶ 16 መጻሕፍትን ማሰባሰብ እንደቻለ ተናግሯል።
የተሰበሰቡት መጽሐፍት በዋናነት በህግ ማዕቀፎችና ህግ ነክ ጉዳዮች፣ በታሪክና ፍልስፍና፣ በሳይንስና ፈጠራ፣ በቢዝነስ በሳይኮሎጂ፣ በግለ-ታሪኮች እና በልቦለድ ዘውጎች ላይ ያተኮሩ ስለመሆናቸው ጠቁሟል።
ማህበራዊ ሚዲያ በንትርክና ፀብ ከሚጭሩ አጀንዳዎች በማውጣት ለእንደዚህ ዓይነት በጎ ተግባር መጠቀም እንደሚቻል የገለፀ ሲሆን የአሁኑ ትውልድ መጽሐፍት እንዲያነብ መስራትና ምቹ የማንበቢያ አካባቢን መፍጠር ትውልድ ላይ መስራት እንደሆነ አክሏል ጋዜጠኛ አብርሃም።
የመጽሐፍትና መሰል ድጋፎችን የማሰባሰቡ ተግባር ቀጣይነት ያለው ስለመሆኑ የገለፀው ጋዜጠኛው ሌሎች ግለሰቦች፣ ተቋማትና በጎ አድራጊ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ ቢያደርጉ በተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን ማቅለል ይቻላል ብሏል።
የሆሳዕና ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘውዱ ዱኖሮ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ስልጣን ካላቸው ፍርድ ቤቶች ወሳኔ ያገኙ ታራሚዎችን በማረምና በማነጽ ረገድ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በክህሎት በቅተው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ በጓሮ አትክልት፣ በቀለም ትምህርት፣ በዕደ-ጥበባት፣ በእርባታዎች፣ በብረታ ብረት፣ በቆዳና ሌጦ እዲሁም በሐር ትል ስራ እና በመሰል ዘርፎች እየተሳተፉ ይገኛል ብለዋል።
መጽሐፍት ሁነኛ የአዕምሮ ምግብ ናቸው ያሉት ዋና ኢንስፔክተር የተደረገው የመጽሐፍት ድጋፍ ታራሚዎች ሰፊ ዕውቀት እንዲሸምቱ ስለ ህግ ነክ ጉዳዮች ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ተቋሙን ለታራሚዎች ምቹና ስብዕናቸውን የሚገነቡበት ጭምር ለማድረግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ለ(ICT)ማዕከል እንደ ኮምፒውተር፣ መጻሕፍት መደራደሪያ ሼልፍ፣ ወንበርና ጠረጴዛ ያሉ መሰል ቁሶች እጥረት እንዳሉ አስረድተዋል ዋና ኢንስፔክተሩ።
በተቋሙ ባለው ቤተመጻሕፍት ማዕከል ያገኘናቸው አንዳንድ ታራሚዎች በበኩላቸው ታራሚዎች ታንፀው እንዲወጡ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን አውስተው የተደረገው የመጽሐፍት ድጋፍ ታራሚዎች ተጨማሪ ዕውቀት እንዲገበያዩና የአስተሳሰብ አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ከፍተኛ እገዛ ያላቸው ስለመሆናቸውም አስገንዘበዋል።




5 comments
ሁላችሁም አንብቡ ስታነቡ የሚቀየረው ድንቁርና ብቻ ነው 👐
አብርሽ ጥሩ ስራ ነው
ምጥ ሰው 👌👌👌
እንደዝህ ፓርላማ ወስደው ብሰጥልን በነካ እጁ
ጋዜጠኞች በተለይ የሚዲያ ስራ ከመዘገብ ጎን ለጎን በእንደዚህ አይነት በጎ ተግባር መሳተፍ አለባቸው ለዚህ ደሞ Abraham Mugoro አርያ ሰብ ነው ❤👏👏
ይሄ ማህበራዊ ሚዲያ እያለ መቼም አናነብም አንደኛውን ማረሚያ ቤት ስንገባ እናነባለን ጥሩ ሥራ ነው 👍👍👍🤪🤪🤣🤣🤣