
ቅዱሳን መላእክት ምግባቸው ምስጋና፣ ምስጋናቸው ምግብ ሆኗቸው የሚኖሩ ከእሳትና ከነፋስ የተፈጠሩ ዘለዓለማዊ ረቂቃን መናፍስት ናቸው፡፡
የአምላካችን የእግዚአብሔርን ኃያልነት ይህን ያህላል ይህንንም ይመስላ ብለን ልንናገር የማንችለው መሆኑን ከሚያሳዩን ነገሮች አንዱ እነዚህ ረቂቃን፣ ኃያላን የሆኑ ፍጡራን የሚገዙለት መሆኑ ነው፡፡ ዘጠና ዘጠኝ ነገደ መላእክት ብለን እንናገር እንጂ በየነገዱ ስር ያሉት ቆጥረን የማንዘልቃቸው፣ እልፍ አእላፋት ናቸው፡፡
ከእነዚህ ነገዶች አንዱ ሱራፌል ወይም ሃያ አራቱ ካሕናተ ሰማይ ናቸው፡፡ የዚህ ነገድ አንዱ መልአክ ሱራፊ የሚባል ሲሆን ሱራፌል የሙሉ ነገዱ ስም ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ካህናተ ሰማይ በመባል ይጠራሉ፡፡ በዘመነ ኦሪት በሰው አምሳል በመገለጣቸውም ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል፡፡
በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሳያርፉ፣ ሳያቋርጡ የሚያጥኑት ካህናተ ሰማይ ምስጋናቸው ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ፡፡ በቅድስት ሥላሴ ስዕል ዙሪያ ከምናያቸው ገጾች ውስጥም ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳ ከኪሩቤል ነገድ፣ ገጸ ንስርና ገጸላሕም ደግሞ ከሱራፌል ነገድ ካሉ መላዕክት በመውሰድ ፊታቸውን ወደ ውጪ ጀርባቸውን ወደ ውስጥ አዙረው መንበሩን እንዲሸከሙ አድርጓል፡፡ ይህም የእርሱን የፈጣሪያቸውን ፊት ማየት እንደማይቻላቸው ሲነግራቸው ነው፡፡
ሃያ አራቱ ካሕናተ ሰማይ ደግሞ መንበሩን እየዞሩ ያጥናሉ፡፡ ራዕይ 4÷6 እና 5÷8 ላይ እንደተጻፈው “ዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ፡፡” ይህም ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድ ላይ ባለበት በዙፋኑ ይሰግዱለታል የሚለውን እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
ይህ ምስጋና የማያቋርጥ፣ ዘመን የማይገድበው፣ የወቅቶች መፈራረቅ፣ የፀሐይና የጨረቃ መመላለስ የመይገድበው ነው፡፡ በሃያ አራቱ ካሕናተ ሰማይ ምሳሌነት በምድር ያሉ ካሕናት በቅዳሴ ጊዜ መንበሩን እየዞሩ በማጠን አምላካችን እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ “መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ፡፡” እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “ልዩ ሦስት ለሚሆኑ ለሥላሴ ምስጋናና ክብር ይገባል” እያሉ በመስገድ የዙፋኑ ምሳሌ የሆነውን መንበሩን ያጥናሉ፡፡ ሕዝቡም እውነት ነው ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ይላሉ፡፡
ይህ ምስጢር የሚፈጸምባት ቅዳሴው ውዳሴው የሚካሔድባት ቤተ ክርስቲያን ስትፈርስ፣ ገዳማትና ገዳማውያን ሲቸገሩ ማገዝ የዚህ ድንቅ ምስጢር በረከት ተካፋይ መሆን ነው፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ በለሳ ወረዳ በሚገኘው ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አድነት ገዳም ከዘጠና በላይ ገዳማውያን መነኮሳት ይኖራሉ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን አባቶች እናግዝ ገዳማቸውን እናጽና ስብሐተ እግዚአብሔር የሚደርስበት ቤተ ክርስቲያኑንም እናንጽ፡፡
ድጋፍ ለማድረግ :-ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
ለተጨማሪ መረጃ:-
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957
ወይም 0938644444