በሲናና ወረዳ ወልቲኢ አርጆ ቀበሌ ነዋሪ እና የሁለት ልጆች ወላጆች የሆነዉ ጎሳ በላቸው ከኮከቤ ዳምጤ ጋር ትዳር መስርቶ አብረው ሲኖሩ የቆየ ቢሆንም በአካባቢያቸው ያሉ ሴቶች አረብ ሀገር ሄደው ሰርተው ሲመጡ በመመልከት እኔም መሄድ አለብኝ በሚል ጥያቄ በመካከላቸው ግጭት ይፈጠር የነበረ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም በተፈጠረ ግጭት ወደ ቤተሰቦቿ ጋር ኮከቤ ዳምጤ ትሄዳለች፡፡ ባለቤቷ ሳያውቅ በድብቅ ወደ አረብ ሃገር ለመሄድ የሚያስፈልጋትን ዝግጅት ትጀምራለች ። ሀምሌ 28ቀን 2016 ዓ.ም ኮከቤ ዳምጤ ወደ ቀበሌ በመሄድ የልደት ካርድ ስታወጣ ለባለቤቷ መረጃው ይደርሰዋል ። ይህንንም ሲሰማ በመበሳጨት ስለታም ባንጋ በመያዝ ከቀበሌ ስትመለስ የበቆሎ እርሻ ውስጥ ጠብቆ ሃሳቤን አላከበርሽም በማለት የጆሮ ግንዷን መቶ ከጣላጥ በኋላ ግራ እጇን ሙሉ በሙሉ መቁረጡ ተገልጿል ።
ስትጮህ የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጎጂዋን ወደ ሮቤ ሆስፒታል በመውሰድ እርዳታ እንድታኝ አድርገዋል፡፡ ፖሊስ ጉዳቱን በመመልከት ተከሳሹን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን በማጣራት ለዓቃቢህግ ይልካል። ዓቃቢህግ ሰው በመግደል ሙከራ እና በአካል ማጉደል ክስ በመመስረት ለፍርድ ቤት ያቀርባል ።
የባሌ ዞን ፍርድ ቤትም ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ጎሳ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ15 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑን የሲናና ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ፍቅሩ ቦጃ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
