banner

‹‹የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ባልተረጋገጠበት ስለ እግር ኳስ ዕድገት ማሰብ ከባድ ነው›› ጋሻው አብዛ (ዶ/ር)፣ በሰሜን አሜ

‹‹የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ባልተረጋገጠበት ስለ እግር ኳስ ዕድገት ማሰብ ከባድ ነው›› ጋሻው አብዛ (ዶ/ር)፣ በሰሜን አሜሪካ የታውሰን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ከመንግሥት ጥገኝነት ተላቀው ኅብረተሰብ አቀፍ ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይችሉ ዘንድ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር በመተባበር ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ፣ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት፣ በማስረጃና መረጃ ላይ የተመሠረተ ጥናት አስጠንተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ታውሰን ዩኒቨርሲቲ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ በርካታ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን የሚሳተፉበት፣ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በኖቫ ኮኔክሽን ሥር ሆኖ የሚካሄደው ግራንድ አፍሪካ ራንና አፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥርተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች በስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ላይ የማማከር ሥራን ጨምሮ ዘርፉን ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ጨምሮ ከ85 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል፡፡ ጋሻው ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እያከናወኑት ያለውን የሩጫና የበጎ አድራት ድርጅትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መዋቅራዊ ቁመና ዙሪያ ከጥናቱ በመነሳት ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ከለቀቁ በኋላ ‹‹ግራንድ አፍሪካ ራን›› የተሰኘ ሩጫን መነሻ ያደረገ ድርጅት በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ላለፉት ስድስት ዓመታት የሩጫ ውድድር አካሂደዋል፡፡ ውጤቱን እንዴት አገኙት?

ዶ/ር ጋሻው፡- ግራንድ አፍሪካ ራን በኖቫ ኮኔክሽን ሥር ሆኖ ለትርፍ ያልተቋቋመ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ ከሩጫው ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ስፖርቱን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ ታላላቅ ሰዎች ዕውቅና በመስጠት ላይ የሚገኘው አፍሪካ ኢምፓክ አዋርድ አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ ዓላማው ኢትዮጵያን ጨምሮ ምሥራቅ አፍሪካውያን የሚታወቁበት አትሌቲክስን እንደ መገናኛ መድረክ በመጠቀም፣ በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማገናኘትና ማስተዋወቅ ዋነኛው ነው፡፡ ሁለተኛው በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ከባህላቸው ጋር ለማቀራረብና ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ለማድረግና በሦስተኛ ደረጃ ተሻጋሪ ለውጥና ተፅዕኖ የፈጠሩ ሰዎችን ስፖርቱን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ዕውቅና የሚሰጥበትና የሚከበሩበት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ላለፉት ስድስት ዓመታት በተካሄደው ዝግጅት በሩጫውም ሆነ በዕውቅናው ትልቅ ለውጥ አሳይቷል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ለጋሽ እጆችን ለሚሹ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ ተነሳሽነቱና ፍላጎቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የለጋሽ ድርጅቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ይህ ሲባል ግን ዕገዛው ባለው ሁኔታ አጥጋቢና በቂ ነው ባይባልም፣ ገንዘብ እየተሰበሰበ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ተደርጓል፣ እየተደረገም ይገኛል፡፡ እስካሁንም መሠረት መብራቴ፣ ሰለሞን ቦጋለና ቻቺ ታደሰን የመሳሰሉ ለሚያግዟቸው በጎ አድጎት ድርጅቶች ዕገዛው ተደርጓል፡፡ በአሜሪካ ለሚኖሩ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያም ተመሳሳይ ድጋፍና ዕገዛም ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡– አትሌቲክሱን ከማስተዋወቅ አኳያስ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ጋሻው፡- አትሌቲክሱ ላይ ታዳጊዎችን በማፍራት ረገድ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል ማለት ባልችልም፣ ነገር ግን በዚያው በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልጆች በየዓመቱ በሚደረገው የሩጫ ውድድር ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በዚህ ሩጫ ጀምረው በአሁኑ ወቅት በትልልቅ ካምፓኒዎችና ድርጅቶች ታቅፈው በፕሮፌሽናል ደረጃ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ውድድሩ በተደረገባቸው ዓመታት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ከደራርቱ ቱሉ ጀምሮ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ጉዳፍ ፀጋይና ትዕግሥት አሰፋን የመሳሰሉ አትሌቶች በክብር እንግድነት ስለሚጋበዙ፣ የእነሱን አርዓያነት የሚከተሉ ከሁሉም የአሜሪካ ግዛት በውድድሩ ለመሳተፍ የሚመዘገቡ ቁጥራቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስፖርቱ ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አኳያ፣ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ በዓመት አንድ ጊዜ የሚገናኙበት ትልቅ መድረክም ሆኗል፡፡ በዚህም በተለይ ለኢትዮጵያውያን ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳው በራሱ ትልቅ እየሆነ ነው፡፡ አሁን ላይ እንዲህ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም፣ በሆነ ወቅት ግን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተገኘ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በኦሊምፒክ አሊያም በትልልቅ ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ሆኖ የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ካለው ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ስል ዝም ብዬ ሳይሆን፣ የቀድሞ ሯጮች ከነበሩ ቤተሰቦች ከአቶ ገነት ገብረ ሥላሴ፣ ሙሉጌታ ወንድሙና የሌሎችም ልጆች በአሜሪካ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እያሳዩት ያለው ተሳትፎ የብዙዎችን ቀልብ መግዛት ጀምሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ አሜሪካን ወክለው በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ በመካከለኛ ርቀት ውጤታማ የሆኑም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡– የሩጫው ስያሜ ‹‹ግራንድ አፍሪካ ራን›› እንደ መሆኑ በመድረኩ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የአፍሪካውያን ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ጋሻው፡- በርከት ያሉ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በመድረኩ በሚፈለገው መጠን ለማሳተፍ ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡ እንደ ስፖርት ቢዝነስ ባለሙያ (ማርኬተር) አንድን ፕሮጀክት ተቋም ለማድረግ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ አሁን የእኛ ሥረ መሠረቱን በማስፋት ደንበኞችን ማወቅ፣ ተሳታፊህን ማወቅና መለየት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ከተመለከትነው ምንም እንኳ የሩጫው ስያሜ ግራንድ አፍሪካ የሚል ቢሆንም፣ አሁን በቅርበት የምናወዳድረው ኢትዮጵያውያንን ካልሆነ አፍሪካውያን በቁጥር ደረጃ ያን ያህል ነው፡፡ ዕቅዳችን መጀመሪያ ለአኗኗርም ሆነ ለማኅበራዊ መስተጋብር ቅርበት ያላቸው ማኅበረሰቦቻችን ላይ ያተኮረ እንዲሆን ነው፣ በዚያም ተሳክቶልናል ማለት እችላለሁ፡፡ ባለፈው 2024 ባደረግነው ሩጫ ቁጥራቸው ወደ 300 የሚጠጋ አፍሪካውያን ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ የእኛም ፍላጎት ቀስ እያለ ተፈጥሯዊ ዕድገቱን ጠብቆ ቁጥሩ እያደገ እንዲመጣ ነው፡፡ የሚገርመው ቁጥሩ ተፈጥሯዊ ዕድገቱን ጠብቆ እንዲጨምር በምናደርገው በአንድ ጊዜ ከአቅማችን በላይ እንደሚሆን ካለው ነባራዊ እውነታ መገመት አያዳግትም፡፡
ሪፖርተር፡– የአገር ውስጥ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ከኖቫ ኮኔክሽን ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ በቅርቡም ከሁለት የአገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ተፈራርማችኋል፡፡ በዚህ ደረጃ ምን ያህል እምነት እየተጣለብን ነው ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ጋሻው፡- ይህ እንደ አንድ የቢዝነስ ባለሙያ የሚነግረኝ፣ ኢትዮጵያ ወስጥ ከተቋማት ጋር በጋራ መሥራት በአገራችን የተለመደው ስፖንሰር ማድረግ ማለት ዕርዳታ እንጂ አብሮ ለማደግ የሚደረግ ስምምነት ተደርጎ አይወሰድም፡፡ በመሆኑም አሁን እየተፈጠረ ያለው የነበረው የተሳሳተ አስተሳሰብ እየተቀየረ፣ ጥቅሙም የጋራ እንደሆነ እምነት እያሳደረ መምጣቱን ነው፡፡ ከኖቫ ኮኔክሽን ጋር አብሮ ለማሠራት የተስማሙት ዳሸን ቢራና ጎፈሬ አብረውን ለረዥም ጊዜ የዘለቁ ናቸው፡፡ በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ደንበኞቻቸውም ተደራሽ ሆነዋል፡፡ ሌላው በሰሜን አሜሪካም ሆነ በሌላው ዓለም የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉም በልቡ የሚያልመው ኢትዮጵያን ስለሆነ፣ ያንን ታሳቢ በማድረግ የሚፈጸም ስምምነት ጭምር ነው፡፡ ይህ በአገር ቤትም በስፋት ቢለመድ በተለይ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት የሚኖረው ድርሻ ቀላል አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡– ከመደበኛ ሥራዎች በተጨማሪ ሩጫው ላይ እየሠሩ ከመሆኑ አኳያ፣ አገር ቤት የሚገኘውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስን በሙያ ደረጃ ለማገዝና ለመደገፍ ጥያቄ ያቀረቡበት፣ አሊያም ከራሱ ከተቋሙ የቀረበልዎት ሐሳብ ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ጋሻው፡- ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ሌሎችም በቅርበት እንተዋወቃለን፣ እንተጋገዛለን፣ ወዳጆችም ነን፡፡ እንደተባለው አትሌቲክስ የኢትዮጵያውያን ትልቅ ገጸ በረከት ብቻ ሳይሆንም፣ የማንነታችን መገለጫም ነው፡፡ ይህንን ተቋም ለማገዝ ቤታችን ሁሌም ክፍት ነው፡፡ አሁን ላይ ተቋሙ በአዳዲስ አመራሮች ተተክቷል፡፡ ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ካለ በግሌ የምሰስተው ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ አመራሩ በሒደት ከእኛ ጋር አብሮ ለመሥራት፣ በተለይም ማስረጃና መረጃ ላይ የተመሠረተ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ይሆናሉ የሚል እምነት ይኖረኛል፡፡ ስንደርስበት የምንነጋገርበት ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ ተቋሙን በገቢ ከማጠናከር አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተነካ ሀብት ስላለ አብረን እንደምንሠራ ተስፋ አለኝ፡፡ በሰሜን አሜሪካ በዚህ ደረጃ መግለጽ የምፈልገው አትሌቲክስ፣ ባስኬት ቦል፣ ፉትቦል፣ ቤዝ ቦልን ጨምሮ ካሉት 124 ቡድኖች መካከል 95 በመቶዎቹ ማዘውተሪያዎቻቸው (ስታዲየሞች) መጠሪያቸው፣ የባንክና የተለያዩ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ትጥቅ አምራች ኩባንያዎችና ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ በግንባታ ላይ የሚገኘውን አደይ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ ብዙዎቹ ማዘውተሪያዎች መጠሪያቸው የቢዝነስን ዕሳቤ ከግምት ያስገባ አይደለም፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ስፖርት ዕድገት የምንፈልግ ከሆነ መቀየር ያለበት አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል በሰሜን አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ‹‹ቢት ኮይን›› የተሰኘው ኩባንያ ማዘውተሪያዎች (ስታዲየሞች) በስሙ እንዲሰየሙ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ነው ለስፖርት ክለቦች አሊያም ቡድኖች የሚከፍለው፡፡ በዚያው በሰሜን አሜሪካ ኢስኮሽያ ባንክ የተሰኘው ተቋም እንዲሁ የስታዲየሙ ስያሜ በስሙ እንዲጠራ በዓመት 40 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል አውቃለሁ፡፡ የብዙዎቹ ኮንትራት ትንሹ ዓመት ሲሆን ትልቁ ደግሞ 30 ዓመት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው አደይ አበባ ስታዲየም ከምንለው ‹‹ሲቢኢ›› ስታዲየም ብለን የማንሰይመው ለምንድነው? ይህንን ወደ አትሌቲክሱ ወስደን በገንዘብ ችግር ወደ መሬት ባንክ ከዓመታት በፊት እንዲመለስ የተደረገው የሰንዳፋ አትሌቲክስ መንደር ‹‹ናይኪ›› አሊያም በሌላ በሚታወቅ ካምፓኒ ስም የማንሰይመው ለምድነው? ይህ ብዙ ማሰብ የማይጠይቅ ፊት ለፊት የምናገኘው የአደባባይ እውነታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ አንድ ጥናት አስጠንተው የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጥናቱ ውጤት ምን ላይ ደርሷል ብለው የሚከታተሉበት ሁኔታ አለ?

ዶ/ር ጋሻው፡- እከታተለዋለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለዚያ ጥናት ነገሮችን በማመቻቸት ተነሳሽነቱን ላመቻቹልኝ አካላት ማለትም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርና ክለባት ከፍ ያለ ምሥጋና አለኝ፡፡ በተለይ ሁለቱ ተቋማት ፌዴሬሽኑና ፕሪሚየር ሊጉ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ የዳኞች አስተዳደደር፣ የተጫዋቾች አስተዳደር፣ የአሠልጣኞች፣ እንዲሁም ገቢና ወጪን በሚመለከት ያላቸው የሥልጣን አንድነትና ልዩነት በተለይም ሊጉ ራሱን ችሎ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የወሰዱት ተነሳሽነት በጣም የሚገርምና የሚበረታታ ሊያድግ የሚችል ነው፡፡ ሊጉን በሚመለከት የጋሻው ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ የጥናት ቡድኑ በማስረጃና መረጃ ላይ የተመሠረተ ግኝት፣ መሬት ላይ ያለ እውነት ነው፡፡ ከግኝቱ ተነስተው በግኝቱ መፍትሔ ላይ በበቂ ሁኔታ ሄደንበታል ወይ? ጅምር እንደመሆኑ ሁለትና ሦስት ዓመት መጠበቅ ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ነገር ግን እንደ ሥጋት የምናገረው አሊያም የመንግሥት ትኩረት ያስፈልገዋል የምለው የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ነው፡፡ ይህ የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ሺሕ ጊዜ ቢጠና የትም መድረስ አይችልም፡፡ የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ሲባል ለምሳሌ ሲዳማ፣ ወላይታና ባህር ዳርን ብንወስድ በጀታቸው በሙሉ ለሕዝብ መሠረታዊ ፍጆታ የሚውል ማለትም ለጤና፣ ለትምህርት አሊያም ለመንገድ አገልግሎት የሚውል ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሁን ለሚለው ክለቦቹ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት ብቃቱም አቅሙም አላቸው፡፡ ምንድነው? ካልከኝ አሁንም ደግሜ ደጋግሜ ልነግርህ የምችለው ምንድነው፣ ተወደደም ተጠላ ክለቦቹ ወደ ግል ይዞታነት በመቀየር ማኅበረሰብ አቀፍ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በጥናቱ የብዙ አገሮች ተሞክሮ ተወስዶ ለኢትዮጵያ የሚበጀው ነው የተወሰደው፡፡ ማለትም መንግሥት ራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል፣ ከዚያም ባለሀብት፣ ኅብረተሰቡና ደጋፊው (የተመዘገበ) ናቸው፡፡ ባለሀብት ሲባል አቪዬሽን አሊያም ቴሌኮም፣ በውጭ የሚኖር ባለሀብት (ዳያስፖራ) አሊያም አገር ውስጥ የሚገኝ ባለሀብት፣ እንደ ድርሻቸው በመቶኛ ተከፋፍሎ የባለቤትነት ድርሻቸውን በሕግ አግባብ ማስቀመጥና ከድርጅቱ አሊያም ከክለቡ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ተጠያቂነቱም አብሮ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ባለፈው ዓመት በጥናቱ ግኝት መሠረት ማኑዋሎችና መመርያዎች ተሠርተው ለሚመለከታቸው ሁሉ ተደራሽ ተደርገዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የተለያዩ ገቢ ማሰባሰብ ላይ፣ ከባህር ዳርና ከፋሲል ከተማ ክለቦች ጋር እነዚህን ማኑዋሎችና መመርያዎች ላይ የመሥራት ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ ብዙም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በሁሉም ዘንድ ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ አለ፡፡ ችግሩ ምንድነው ካልከኝ አሁንም የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ገና ስላልተረጋገጠ ዕውን ማድረግ አልቻልንም፡፡ ስለሆነም የባለቤትነት ይዞታው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡– በጥናቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡ የባለቤትነት ይዞታ የሚለው የጥናት ግኝቱ አንድ አካል ነው፡፡ ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለው ለምን ይመስልዎታል?

ዶ/ር ጋሻው፡- በግሌ ተጠያቂው አበበ ወይም ከበደ ነው ማለት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ለጥናት ግኝቱ መተግበር ሁሉም በጋራ ሊሠሩበት ይገባል ማለት ግን እወዳለሁ፡፡ ይህን ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት መፍትሔ ስለሌለው ማለቴ ነው፡፡ ተግባራዊ ከተደረገ ግን የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መመርያን ጨምሮ ተጫዋቾችና የባለድርሻ አካላት ወርኃዊ ክፍያ እንደ አቅም ለመክፈል ቀላል ይሆናል፡፡ ባለው ሁኔታ ግን የመንግሥትን ገንዘብ ዝም ብሎ መክፈል አሸዋ ላይ ውኃ ከማፍሰስ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የክለቦች የትኬት (ሜዳ) ገቢ፣ የስፖንሰርሺፕ፣ የስታዲየም ውስጥ የስፖርት አልባሳት (ጀርሲዎች) የሚገኘውን ጨምሮ ከምግብ ሽያጭና ከመሳሰሉት የሚገኙ የገቢ ምንጮች አግባብ ባለው ማኑዋልና መመርያዎች ሊተዳደሩ የሚችሉት ቀደም ሲል ለመናገር እንደሞከርኩት የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ባልተረጋገጠበት ስለእግር ኳስ ዕድገት ማሰብ ከባድ ነው፡፡

2 comments

Natinael Nega January 20, 2025 - 8:09 am

ፅሁፈን ጨርሽ ነው ያነበብኩት😡

Reply
Degife Shugute January 20, 2025 - 8:15 am

ፅሁፉን የጨረሳቹ, እስት እጃቹን ወደላይ🙄

Reply

Leave a Comment