banner

#ከታላላቅ ከተሞች ሁሉ ክብሯ ከፍ ያለው ረቂቅ ከተማ

“የቅድስት ሥላሴን ስዕል ስንመለከት ዓለምን በመሀል እጃቸው ይዘዋት እናያለን፡፡ በዘመነው አጠራር ዩኒቨርስ የምንለው የሰው ልጅ እውቀት የደረሰበት ፕላኔቶችና ብርሃናት ሁሉ በሥላሴ መሀል እጅ ላይ ከተያዙ፣ እነርሱ የት ሆነው ነው?” ከሚለው በመነሳት የእግዚአብሔር ምላትና ወሰን በሰው አእምሮ የማይመረመር፣ የማይነገር መሆኑን በተረዳ ነገር ሊቃውንት አባቶቻችን ያስተምሩናል፡፡ ይህን ድንቅ የእግዚአብሔር የባሕርይ አምላክነት ስናውቅ ነው የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ገናናነት የምናደንቀው፡፡ ሁሉ በእጁ የተያዘ እርሱን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በድንግልና ማሕጸኗ ወሰነችው፡፡ የ15 ዓመት ታናሽ ብላቴና ስትሆን ለታላቅነቱ ወደር የሌለው እርሱ ማደሪያው ትሆን ዘንድ የሚመርጣት ሆና ተገኝታለች፡፡

ለዚህም ነው ቅድስት ድንግል ማርያም በሉቃስ 1÷49 “ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ፍጥረት ዅሉ ያመሰግኑኛል” በማለት የተናገረችው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም “አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ብሏታል” ሉቃስ 1÷28፡፡ ለአዳምና ለኛ ለልጆቹ የተገባው ቃል ኪዳን የተፈጸመው በቅድስት ድንግል ማርያም ለመለኮት ማደሪያነት ምቹ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በባሕርዩ ንጹህ የሆነው እርሱ ባደፈ አካል ውስጥ አያድርምና፣ ዓለም ሁሉ በበደለበት በዚያ ወራት እርሷ ብቻ ንጽሕት ሆና ተገኝታለች፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም “አብ ከሰማያት ሆኖ ቢያይ፣ እንዳንቺ ያለ አላገኘም፣ አንድያ ልጁንም ሰዶ ሰው ሆኖ አዳነን” የሚለን፡፡

ዓለምን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛው እርሱ ማሕጸኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በዚያ ተወሰነ፡፡ ከታላላቅ ከተሞች ሁሉ ክብሯ ከፍ ያለ ረቂቅ ከተማ ናትና መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን በቅድሰት ድንግል ማርያም ላይ የማደሩ ምሥጢር በነቢያት፣ በሐዋርያት ላይ ያነጻቸው፤ ይቀድሳቸው፤ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ እንዳደረው ዓይነት አይደለም፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ሆነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በወንጌሉ 1÷45 ላይ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት ገልጾታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ ምስጢሩንና ጥበቡን አምልቶና አስፍቶ የገለጸላቸው አባቶቻችን እግዚአብሔር ዓለሙን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰው ሆኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል ብለው ያስተምራሉ፡፡ በድንግል ማሕጸን ባደረ ጊዜ ዙፋኑን በወዴት ዘረጋው? እልፍ አእላፍ መላእክት በዙሪያው ምስጋናቸውን አላቋረጡምና በወዴት ሆነው አመሰገኑት? ይህ ድንቅ ምስጢር የተፈጸመባት ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው አምላክ፣ አምላክም ሰው እንዲሆን ምክንያት ሆነች፡፡ ለዚህም ነው ገዳማውያን አባቶች ከፈጣሪ በታች ከፍጥረት ሁሉ በላይ የሆነች እርሷን የአምላካችን እናት ከልጇ ከወዳጇጋር ያለማቋረጥ እንደ መላዕክት የሚያመሰግኗት፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444

Leave a Comment