#FastMereja I ሄኖሲስ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር 25,000 ሴቶችና እናቶችን አሰልጥኖ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ ለማስቻል 1.5 ቢሊየን ብር በጀት የተመደበለት ፕሮጀክቱን ዛሬ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በዌስተርን ፕላስ ሆቴል አስመረቀ፡፡
የፕሮጀክቱ መሪ ሃሳብ “Access to Work and Financial Inclusion for Women” የሚል ሲሆን በቤታቸው ሆነው ልጆች በማሳደግ ላይ ያሉ እናቶችን ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በተጨማሪም ሌሎች የራሳቸውን ስራ መስራት የሚፈልጉ ሴቶችን ይጨምራል፡፡ ፕሮጀክቱ በስፕሪንግ ፊልድ ትምህርት እና ማህበራዊ ጉዳዩች ስልጠናና ማማከር የሚመራ ሲሆን ሄኖሲስ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ደግሞ ስልጠናውን በስኬት እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ባሻገር የፋይናንስ አቅርቦትም ያደርጋል፡፡
ይህን የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም የከፈቱት የህብረት ስራ ማህበሩ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዙፋን ጋሻው ሲሆኑ በንግግራቸው ላይ ይህ የሄኖሲስ ፕሮጀክት ለህብረተሰቡ አጋር መሆናችንን የምናረጋግጥበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ሄኖሲስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመራጭም አማራጭም መሆን የቻለ ህብረት ስራ ማህበር ሲሆን አባላትን ምቹ እና ዘመናዊ በሆነ ቢሮው እያገለገለም ይገኛል፡፡




