#FastMereja I አሜሪካ ሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን መምታቱን ተናግራለች። እነዚህም ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋሃን ናቸው።
ፎርዶ ከዋና ከተማዋ ቴህራን በስተደቡብ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ የሚገኝ ከመሬት በታች በጥልቅ ዋሻዎች ውስጥ የተሸሸገ እንደሆነ ይታመናል።
ፎርዶ ከምድር በታች ያለው ጥልቀት እስራኤል ባሏት የጦር መሳሪያዎች ለመድረስ አስቸጋሪ ነው።
ፎርዶን ለማውደም የሚያስችል ጠንካራ እና ትልቅ “ምሽግ ደርማሽ” ቦምብ እንዳላት የሚታመነው ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ናት።
አሜሪካ ያላት ቦምብ ጂቢዩ-57 ማሲቭ ኦርዲናንስ ፔኔትሬተር (ኤምኦፒ) ይባላል።
ክብደቱ 13,000 ኪ.ግ ሲሆን ባለሙያዎች ከመፈንዳቱ በፊት ወደ 18 ሜትር ኮንክሪት ወይም 61 ሜትር መሬት ውስጥ ዘልቆ መግባት ይችላል ይላሉ።
የፎርዶ ዋሻዎች ከመሬት በታች ከ 80 እስከ 90 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኙ ይታመናል።
ስለዚህም ኤምኦፒ ውጤታማ በሆነ መልኩ ያወድመዋል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም።
ነገር ግን ተቋሙን ለማውደም ሊቀርብ የሚችለው ብቸኛው ቦምብ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በጥቃቱ ወቅት ኤምኦፒን ጥቅም ላይ መዋሉን ለሲቢኤስ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ዒላማ ሁለት ሁለት ቦምቦች ተጠቅመዋል።
📌 በኢራን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?
የአሜሪካ ጥቃት በኒውክሌር ተቋማቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት፣የሰው ሕይወት ስለማለፉ ወይንም ጉዳት የደረሰበት ስለመኖሩ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ምክትል የፖለቲካ ዳይሬክተር ሐሰን አቤዲኒ ኢራን እነዚህን ሦስት የኒውክሌር ጣቢያዎች “አስቀድማ” ለቅቃ መውጣቷን ተናግረዋል።
በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው ኢራን “ቁሳቁሶቹ ቀደም ብለው ስለወጡ ትልቅ ጉዳት አልደረሰባትም” ብለዋል።
ትራምፕ በቴሌቭዢን ቀርበው ባደረጉት ንግግራቸው “የኒውክሌር ማበልፀጊያ ተቋሞቹ ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል” ብለዋል።
የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ማርክ ኪምሚት ለቢቢሲ ሲናገሩ ግን የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ መርጠዋል።
“እስከ መጨረሻው ወድሟል ብሎ ለመገመት ምንም መረጃ የለም” ነበር ያሉት።
ኢራን ከእስራኤል ጋር እያካሄደች ባለችው ጦርነት ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ1,200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጻለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በኢራን ቁልፍ የኒውክሌር ተቋማት ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል የፀጥታ ጥበቃዋን እያጠናከረች ነው።
እስራኤል በመላ አገሪቱ የሕዝብ የደኅንነት ገደቧን አጠናክራለች ሲል የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
አሜሪካ ኢራንን ከደበደበች በኋላ “በትምህርት እንቅስቃሴዎች፣ ስብሰባዎች እና የሥራ ቦታዎች” ላይ የጣለችውን የደኅንነት ገደብ አጥብቃለች።
ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው




3 comments
ኢራን እስቁንጢንጢን አድርጓት ነበር😂👌 በረደላት ወይ?😂
ባዶ ቦታኮ ነው የደበደበችው።
በዙሪያው ያሉ ሰዎችም የተለምዶ ህይወታቸውን ቀጥለዋል።
አይገባሽም ወይ አለ ዘፋኙ😂😂😂😂😂