ሴቶችን እና ወጣቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተገነባዉ ጋለሪ እና ሬስትራንት ተመረቀ
#FastMereja I የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ወጣቶችን እንዲሁም ሴት ሰአሊያንን የሚያበረታታ “እንቁ ጋለሪ እና ሬስቶራንት” በዛሬዉ እለት ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም ተመረቀ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከሚሰራቸው የልማት እና ሴት ተኮር ሀገር አቀፍ ስራዎች መካከል ተቋሙን የማህበረሰብ አለኝታ መሰረት መሆኑን የሚያረጋግጡ የኢኮኖሚ አውታር የልማት ስራዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህ የልማት ስራዎች መካከል በቦሌ ማተሚያ ፊት ለፊት የተከፈተው እንቁ ጋለሪ እና ሬስቶራንት አንዱ እንደሆነ ተገልጿል።
እንቁ ጋለሪ እና ሬስቶራንት ከጅምሩ ጀምሮ በዋጋ ግሽበት እየተንገላታ የሚገኘውን ዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል እጅግ በተመጣጣኝ እና ኑሮውን በሚደግፍ መልኩ የሬስቶራንት አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም ሬስቶራንቱ ባለው ያማሩ ክፍሎች ውስጥ ተሰቅለው ለጉብኝት የሚቀርቡ የወጣቶችን የስዕል ስራዎችን ለገበያ በማውጣት ወጣቶችን በተለይም ሴት ሰዓሊያንን ለማበረታት ታቅዶ የተገነባ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ጋለሪ እና ሬስቶራንት መሆኑን በመክፈቻዉ ስነ ስርአት ተገልጿል።
እንቁ ጋለሪ እና ሬስቶራንት በዋናነት ሴቶችን እና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተገነባ እንደሆነና ሴቶችን በብዙ መስክ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሁም ሴቶች የራሳቸዉን ገቢ እንዲያገኙ ተሳታፊነታቸዉን እና ተጠቃሚነታቸዉን ለማረጋገጥ ታስቦ የተገነባ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አያለች እሸቴ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ሴቶች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑና ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ከ54 በላይ አባል ማህበራንትን ከ8.6 ሚልዮን በላይ ሴቶችን በአባልነት የያዘ አገር በቀል የሲቪክ ፌደሬሽን እንደሆነም ተገልጿል።
#ኹነት




