banner

ለቀድሞ የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ትምህርት ቤት መምህራን እና ሰራተኞች የምስጋና ዝግጅት ተካሄደ

#FastMereja I በ1970ዎቹ በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች የትምህርት አበርክቶ ላደረጉ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች በዛሬዉ እለት ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም የምስጋና መርሃግብር ተካሄደ።

የምስጋና መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው የቤዛ ህይወት ጓደኛማቾች መረዳጃ እድር እንደሆነ ተገልጿል።

የማህበሩ ሊቀመምበር አቶ ብስራት መኮንን እንደገለፁት ምስጋናው የዛሬ 45 ዓመት በፊት ለተደረገ ደግነት፤ ቅንነት፤ አገር መውደድና መስዋዕትነት፤ እንዲሁም ፍፁም አስቸጋሪ በሆነ አካላዊና መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ለተቸረ ጉልበት፤ የአእምሮ ውጤትና ፅናት የቀረበ ነው ብለዋል፡፡

ተመስጋኞቹ ደግሞ የመከራ ሰለባ መሆናቸው ሳያንስ፤ ነጋ ጠባ ሞትና የሞት ወሬ ብቻ በሚሰማበት ከድቅድቅ ጨለማ ሌላ አንዳች ተስፋ በማይታይበት ቦታና ሁኔታ ውስጥ ታናናሾቻቸውን በእውቀትና በተስፋ ለማነፅ የወሰኑና የተባበሩ እህቶች እና ወንድሞች መምህራኖች ነው ብለዋል፡፡

በምስጋና ኘሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት የቀለም ትምህርት እና የሙያ ስልጠና ታሪክ፣ በቀድሞው ጊዜ በትምህርት ዘርፉ የነበረውን ተጽዕኖ፣ የመምህራኑ አበርክቶ እና ፋይዳ ታሪክ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያሉ እና ከባህር ማዶ የሚገኙ የትምህርት ቤቱ መምህራን እና የቀድሞ ተማሪዎች በተለያየ መልኩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የቤዛ ህይወት ጓደኛማቾች መረዳጃ እድር በ1970ዎቹ በህግ ጥላ ስር የነበሩ እና ከእስር በኋላ ባላቸው ህይወት እርስ በእርስ ለመረዳዳት ያቋቋሙት በህግ የተቋቋመ እድር ነው።

#ማህበራዊ





Leave a Comment