#FastMereja I ኢትዮ ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል በዓለም አቀፍ ደረጃ የISO 9001/2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ጀርመን ሀገር ከሚገኝ ተቋም ዓለም አቀፍ እውቅና እና የብቃት ማረጋገጫ ዛሬ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ተቀበለ።
በአዲስ አበባ የሚገኘው ዲ ኪው ኤስ፤ የሠርተፊኬሽን ኦዲት አገልግሎት ሆስፒታሉ የISO 9001:2015 ዓለም አቀፍ የጥራት ማኔጅመንት ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረጉን ለማረጋገጥ ኦዲተሮቹን ገለልተኛ (3rd party) ኦዲት በማከናወን የሆስፒታሉን ብቃት ማረጋገጥ ችሏል።
በዚሁ መሰረት ሆስፒታሉ ከ20ሺ በላይ የሚሆኑ የዲ ኪው ኤስ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ያገኙ ተቋማት በሚመዘገቡበት ዓለም አቀፍ “ግሎባል ዳታቤዝ” ውስጥ የተመዘገበ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥም ISO 9001: 2015 ዓለም አቀፍ ደረጃን ተግባራዊ አድርገው እውቅና ካገኙ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች አንዱ መሆኑ ተነግሯል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሆስፒታሉ ወደውጪ ሀገር የሚያስኬዱ ሕክምናዎች በሀገር ውስጥ ለማከናወን የጀመረውን ጥረት ለማጠናከር የሚረዳው የላቦራቶሪ ዲፖርትመንቱ ሁለት የጥራት ዕውቅና ( የአክሪዲቴሽን ሰርተፊኬት ) ማግኘቱንም ሆስፒታሉ ጥራት አገልግሎት የሚሰጠው ልዩ ትኩረት ያሳያል ተብሏል።
ኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል ከተመሠረተበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት እያከናወነ ሲሆን በተለይ ለልብ ሕሙማን ሕጻናት የነፃ ሕክምና በመስጠት ከፍ ያለ ማኀበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። በመወጣት ላይም ይገኛል።
ሆስፒታሉ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ብቻ በይፋ በገባው ቃል መሰረት 15 ሕጻናት ተገቢውን ሕክምና ያገኙ ሲሆን በተጨማሪ ከዲቦራ ፋውንዴሽን ጋር ባለው የትብብር ስምምነት መሰረት 25 ሕጻናት የተሟላ የጤና ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል Heart to Heart የተሰኘ ፋውንዴሽን ተገቢውን ሕጋዊ የምስረታ ሒደት አልፎ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ተመስርቷል።
ፋውንዴሽኑ በአዲስ አበባ ከተማም በምሥረታ ላይ ይገኛል። የፋውንዴሽኖቹ መመስረት ሆስፒታሉ የልብ ሕሙማን ሕጻናትን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል ተብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሆስፒታሉ የስትሮክ እና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ጋር ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ወደሥራ እንደሚገባ አቶ ብርሃን ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ውጤት የሁሉም የማኔጅመንት ሰራተኛ ትጋት ውጤት መሆኑን በመጠቆም ለጥራት የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከዚህም ጎን ለጎን ዘመናዊ አሠራርን በማስፈንና ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት በማዳበር ለሕክምና ወደ ውጭ ሃገር የሚደረጉ ጉዞዎች እንዲቀንሱ በማድረግ እንዲሁም የሕሙማንን እንግልትና የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ለአገራችን ኢኮኖሚ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በስካይላይት ሆቴል በተከናወነው በዛሬው መርሐግብር ላይ የሆስፒታሉ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን ተድላ ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት፣ ሠራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።




