#FastMereja I እናት ባንክ አ.ማ. አካታች እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት ሂደት ውስጥ ያለውን መሪነት የሚያጎላ ፈር ቀዳጅ እርምጃ በመውሰድ፣ አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን የግብይት አማካሪው በማድረግ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የጾታ ቦንድ ሽያጭ መዋቅር መጀመሩን ይፋ አደረገ፡፡
የእናት ባንክ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኤርሚያስ አንዳርጌ እንደገለጹት፣ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የጾታ ቦንድ ሽያጭ በመጀመር የባንኩን ተልዕኮ ከመወጣት በተጨማሪ፣ በመጻዒው አካታች የፋይናንስ ከባቢ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን በማምጣት ሂደት ውስጥ ጉልሀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። የካፒታል ገበያው ሥነ ምኅዳር፣ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መሪነት ቅርፅ እየያዘ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እናት ባንክ ፈጠራን፣ አካታችነትን እና ዘለቄታ ያለው ልማትን በአንድ ላይ በሚያስተሳስረው በዚህ አዲስ የፋይናንስ ዘመን ውስጥ ቁልፍ ሚና የመጫወት ፍላጎት አለው ብለዋል።
የጾታ ቦንድ ሽያጩ ሴቶች ለሚመሯቸው እና በባለቤትነት ለያዟቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ለኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለግብርና እና ንግድ ሥራዎች እና ጾታዊ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በተመጠጣኝ ዋጋ ለሚቀርቡ የመኖሪያ ቤቶች፣ ለጤና አገልግሎት፣ ለሕፃናት እንክብካቤ እና እንደ ትምሀርት ላሉ ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች የሚሆኑ የረጅም ጊዜ ፋይናንስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል ይሆናል።
የእናት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አስቴር ሰሎሞን በበኩላቸው፣ ይህ ጅምር እናት ባንክ ፋይናንስ የማግኘት ዕድል ላይ ያለውን የጾታ ክፍተት በቀጣይነት ለመድፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉ ሲሆን፣ “የፋይናንስ አቅርቦትን ለሴት ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች እና የማኅበረ ሰብ ክፍሎች በማዳረስ እኩልነት እና እድገትን ለማምጣት አዲስ መንገድ ይከፍታል ብለዋል።
የጾታ ቦንድ ሽያጩ፣ የእናት ባንክ ጾታዊ አካታች የሆነ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ያለውን የግንባር ቀደምነት ሚና ዳግም የሚያረጋግጥ ነው፣ የግሉ ዘርፍ ፈጠራ ሁሉን ዐቀፍ እድገት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም ማስቀጠል እና በኢትዮጵያ የሴቶችን አቅም ማጎልበት እንደሚችል ያሳያል ተብሏል።





1 comment
የጾታ ወንድ