#FastMereja I በፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ የነበረ እና ግብረ አበሮቹ ከባለጉዳይ በተሰጠ ጥቆማ መሰረት በጉቦ መቀበል ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው የወንጀል ምርመራ ሲጣራባቸው ቆይቶ ታሕሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በሙስና ወንጀል ክስ ቀረበባቸው።
ተጠርጣሪዎቹ በወንጀል ተጠርጣሪ የነበሩ ግለሰብ ላይ የወንጀል ክስ እንዳይቀርብ እናደርጋለን በማለት 1 ሚሊየን ብር እንዲከፍሏቸው ሲደራደሩ ይህንን ድርጊት ጠቋሚዎች ለፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በማሳወቃቸው በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት ክትትል በማድረግ ሕዳር 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከግለሰቡ ቤተሰቦች 500,000 ብር ለጊዜው ባልተያዘ ግብረ አበራቸው የባንክ ሒሳብ እንዲገባ አድርገው የጉቦውን ገንዘብ ያስገቡበትን ደረሰኝ ሲሰጡ እጅ ከፍንጅ ሊያዝ ችሏል።
ይህንን ተከትሎ አስፈላጊ እና አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎች በማሰባሰብ የወንጀል ምርመራ ሥራውን በማጠናቀቅ ታሕሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 10 (1) እና (2)ን በመጥቀስ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦባቸዋል።
