banner

ኢትዮ ቴሌኮም በ6 ወራት ውስጥ 85 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

​#FastMereja I ኢትዮ ቴሌኮም የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት (ከሐምሌ 2017 እስከ ታህሳስ 2018) የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ይፋ አደረገ። ኩባንያው በዚህ ግማሽ ዓመት ውስጥ 85.02 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት መሆኑን አስታውቋል።

​የደንበኞች ቁጥር እና የአገልግሎት ስርጸት
​ኩባንያው በአዲሱ “ቀጣዩ አድማስ 2028” ስትራቴጂው መሠረት ባከናወናቸው ተግባራት፣ የአጠቃላይ ደንበኞቹን ቁጥር ማሳደግ ችሏል።

በሪፖርቱ መሠረት፦
📌 ​የሞባይል ድምፅ ደንበኞች፦ በ8.1% በመጨመር 84 ሚሊዮን ደርሰዋል።
📌 ​የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች፦ በ12.7% በመጨመር 49 ሚሊዮን ደርሰዋል።
📌 ​የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች፦ የ19.2% እድገት በማሳየት 934.7 ሺህ ደርሰዋል።
በአጠቃላይ በሀገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት ስርጸት (Teledensity) መጠን 77.1 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

​ከስድስት ወሩ ገቢ ውስጥ የድምፅ አገልግሎት 30.4%፣ ዳታና ኢንተርኔት 28.3% እንዲሁም ቴሌብር 4.9% ድርሻ አላቸው። ኩባንያው በግማሽ ዓመቱ 88.19 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16.02 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው በቴሌብር ዓለም አቀፍ የሐዋላ አገልግሎት አማካኝነት የተገኘ ነው።

​የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 58.61 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 1.94 ትሪሊዮን ብር የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር ተከናውኗል። አገልግሎቱ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን በኢኮኖሚው ውስጥ 6.88 ትሪሊዮን ብር ማንቀሳቀስ መቻሉን ሪፖርቱ ያሳያል።

​ኩባንያው ምንም እንኳን ከፍተኛ የገቢ እድገት ቢያስመዘግብም፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቴሌኮም መሣሪያዎች ሽያጭ (Devices) እና በኢንተርፕራይዝ ሶሉሽን የገቢ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን በሪፖርቱ ጠቅሷል።

​ይህ አፈጻጸም ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠንና የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።




Leave a Comment