banner

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እንግዶች ደማቅ አቀባበል እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

#FastMereja I ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለመታደም የሚመጡ የአፍሪካ መሪዎችንና እንግዶችን “ልቧን ከፍታና እጆቿን ዘርግታ” እንደምትቀበል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመላው ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልዕክት፣ እንግዶቹ እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸውና የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እንዲገለጽ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት አፍሪካውያን ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት ቀንዲልና የአህጉሪቱ የፖለቲካ ራዕይ ማዕዘን ድንጋይ አድርገው እንደሚመለከቱ ገልጸዋል። “እነዚህ ወዳጆቻችን የሰንደቃችንን ቀለማት የሚጋሩ ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በክብር ተቀብሎ በፍቅር ማቆየት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ክብር ዳግም ማሳየት እንዳለባት የጠቀሰው ይኸው መልዕክት፤ ሕዝቡ የአፍሪካ አንድነትን መንፈስና የወል ህልምን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንግዶቹን እንዲያስተናግድ ጥሪ አቅርቧል።

Leave a Comment