#FastMereja I ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት ወደ ድርድር ከመግባት ይልቅ መጠነ-ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት በማድረግ ወደ አዲስ ጦርነት እያመራ መሆኑን አስታወቀ። ፋስት መረጃ ከመግለጫው እንደተመለከተው፣ ድርጅቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጦርነት ደመናውን ለመግታት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል።
ህወሓት በመግለጫው እንዳመለከተው፣ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ግዙፍ የጦር መሳሪያና የሰራዊት ክምችት ወደ ትግራይ አቅጣጫ እያስጠጋ ይገኛል። ይህ እንቅስቃሴ “ሌላ ዙር ደማዊ ጦርነት ለመክፈት የታለመ ነው” ሲል ድርጅቱ የገለጸ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በሰላማዊ ሰዎችና በሰራዊቱ ላይ የተፈጸሙ የአየርና የምድር ጥቃቶች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቁሟል።
ድርጅቱ በመግለጫው ካሰፈራቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የኢትዮጵያ መንግስት ባደራጃቸው ታጣቂዎች አማካኝነት 40 በመቶ የሚሆነውን የትግራይ ህገ-መንግስታዊ መሬት ወሮ በመያዙ፣ ህዝቡ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሞትና ለስቃይ መዳረጉን ገልጿል።
ህወሓት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም ፍላጎቱ ወደ ጦርነት መግባት ሳይሆን የፕሪቶርያው ስምምነት ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሸጋገር መሆኑን ገልጿል።
ማህበረሰቡ እስካሁን ለቀረቡ የሰላም ጥሪዎች “ጆሮ ዳባ ልበስ” ማለቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታት፣ በአፍሪካ ህብረትና በአሜሪካ በኩል የወጡ መግለጫዎች ጥሩ ጅምር ቢሆኑም፣ አሁን ካለው ስጋት አንጻር ግን “ተጨባጭ እርምጃ” እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
በመጨረሻም ህወሓት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደራዊ ዝግጅቱን በአስቸኳይ አቁሞ ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመለስ ሲል በመግለጫው ገልጿል።
