#FastMereja I የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ እና የዉመን ፎር ዉመን ኢንተርናሽናል በአፍሪካ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ለማራመድ እና በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመፍታት የሚያስችላቸዉን ስልታዊ አጋርነት በይፋ ጀመሩ።
ይህ አጋርነት ይፋ የሆነው የካቲት 5 ቀን 2026 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄደው 39ነኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በተዘጋጀ የኔትወርክ እና የአቀባበል መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡
አጋርነቱ በዋናነት የሴቶችን የኢኮኖሚ ነፃነት ማረጋገጥ፤በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን (GBV) መከላከል፤ሴቶችን በአህጉሪቱ የለውጥ መሪዎች እንዲሆኑ ማብቃት ላይ ያተኩራል።
በአሁኑ ወቅት በመላው አፍሪካ በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት እና ግጭቶች በአህጉሪቱ ላይ በየዓመቱ የ18 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ እያደረሱ እንደሚገኙ እንደሚገመት ይህ ኪሳራ የሚመጣው በከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ፣ በምርታማነት መጥፋት እና በሰብአዊ ቀውሶች ምክንያት እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ።
እንዲሁም ጥናቱ እንደሚያመለክተዉ በአፍሪካ 38% የሚሆኑ ሴቶች አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።
PAUDA-NEPAD ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ናርዶስ በቀለ እንደገለፁት”የምንፈልገው አፍሪካ በስጦታ አይሰጠንም፤ በእሱ ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ መንከባከብ እና የራሳችን ማድረግ እንዳለብን እና ብዙ የአፍሪካ ሴቶች ለለውጥ ዝግጁ ቢሆኑም ስርዓቱ ግን በሩን ዘግቶባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የዉመን ፎር ዉመን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ቴልማ ኤኪዮር በበኩላቸዉ “ሴቶች ግጭትን ተቋቁመው እንዲተርፉ ብቻ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ለውጥ እንዲመሩ የሚያስችል ዘላቂ ስርዓቶችን መገንባት እንዳለበት ገልፀዋል።
ውመን ፎር ውመን ድርጅት ከዚህ ቀደም ከ616 ሺህ በላይ የጦርነት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን መርዳቱ ተገልጿል።




