#FastMereja I በአዳማ ሪጅን አርሲ ዞን ጄጁ ወረዳ በሚገኘው “ተስፋ ሕይወት” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለመስኖ አገልግሎት ይውል የነበረ ትራንስፎርመር በዘራፊዎች መወሰዱ ተገለጸ።
የአዳማ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ጣሃ አህመድ እንደገለጹት፣ ስርቆቱ የተፈጸመው ትላንት የካቲት 5 ቀን 2018 ዓ.ም ከሌሊቱ 5 ሰዓት አካባቢ ነው። የተሰረቀው ትራንስፎርመር 200 ኪ.ቮ.አ/15 ኪ.ቮ.አ አቅም ያለው ሲሆን፣ በወቅቱ ለመስኖ ስራ ይውል የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ይህ አይነቱ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸም ስርቆት የአካባቢውን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ እየጎዳ ይገኛል። በተለይም አርሶ አደሩ በመስኖ በመታገዝ ለሚያከናውነው የምርት ተግባር ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት፦
ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአካባቢው ነዋሪዎች እና የፀጥታ አካላት በጋራ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።
ድርጊቱ በሕግ የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ ሕብረተሰቡ መሰል የጥፋት ተግባራትን ሲመለከት በፍጥነት ለሕግ አስከባሪ አካላት እንዲያሳውቅ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረተ-ልማቶችን መጠበቅ የሁሉንም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አሳስቧል።
