#FastMereja I ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው መግለጫ፣ በሀገሪቱ እየታየ ያለው የሰላም እጥረት እና የማንነት ጥቃት እጅግ እንደሚያሳስበው ገለጸ።
ድምፃዊው መጀመሪያ የክብር ሰላምታውን በማስቀደም፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ለታሪካዊውና አንጸባራቂው የዓድዋ ድል በዓል በታላቅ ብሄራዊ ኩራት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል። ይህ በዓል የኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት መሆኑን በመጥቀስ ብሄራዊ ኩራቱን ገልጿል።
በመግለጫው ላይ ቴዲ አፍሮ በሀገሪቱ ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በዝርዝር አንስቷል።
በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቅሷል።
ለዚህ ማህበራዊና ሀገራዊ ቀውስ ዋነኛው መንስኤ ለዓመታት ስር የሰደደው የዘር ፖለቲካ መሆኑን በአፅንኦት ገልጿል። በግፍ እየሞቱ ላሉና ትኩረት ለተነፈጉ ንፁሃን ዜጎች “ፍትህ” ይገባቸዋል ሲል ድምጹን አሰምቷል።
ድምፃዊው ኢትዮጵያውያን ከዘር እና ከሃይማኖት ልዩነት ወጥተው በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል። ለጋራ ህልውና ስጋት የሆነውን የዘር ፖለቲካ ስርዓት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃ ልንለው ይገባል” ሲል አሳስቧል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት በፀሎት እንዲያስቡም ጠይቋል።
