banner

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ለ50 ሺህ ሕጻናት የሕይወት ተስፋ ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር አዘጋጀ!

#Fastmereja I ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ ከበጎ ፈቃደኛ ሴት ጋዜጠኞች፣ ደራሲያንና ምሁራን ጥምረት ጋር በመሆን “የእኔም ልጆች ናቸዉ “በሚል መሪ ቃል ለከፋ ችግር ለተጋለጡ 50 ሺህ ሕጻናት የሚውል ልዩ የቤተሰብ ስፖንሰርሺፕ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር መዘጋጀቱ በዛሬዉ እለት ተገልጿል።

ይህ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ከነገ የካቲት 27 እስከ መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን ተገልጿል።

የችግሩ ስፋትና የመርሃ-ግብሩ መነሻ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ሳቢያ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ መለየታቸውን መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።

ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቀልበስ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ካለው የረጅም ጊዜ የቤተሰብ ስፖንሰርሽፕ ልምድ በመነሳት፣ በአምስት ክልሎች (በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊያ እና አፋር) ለሚገኙ እጅግ ተጋላጭ ሕጻናት ድጋፍ ለማሰባሰብ ተነስቷል።

ይህንን ጥሪ የተቀበሉ ሴት ጋዜጠኞች፣ ደራሲያንና ምሁራን ባቋቋሙት ጥምረት አባላትቱ አስቀድመው ከ100 በላይ ሕጻናትን በራሳቸው ስፖንሰር ለማድረግ ቃል በመግባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች የሚገኙ ሲሆን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና ተቋማት የልጆችን የኑሮ ዋስትና ለመሸፈን ቃል የሚገቡበትም ነዉ፡፡

ይህ ድጋፍ ሕጻኑ/ኗ ከቤተሰቡ ሳይነጠል መሰረታዊ ፍላጎቶችን (ምግብ፣ ጤና) እንዲያገኝ፣ በትምህርት ገበታው እንዲቆይና ለቁም ነገር እንዲበቃ፣ በማንነቱ የሚተማመንና ጤናማ ዜጋ ሆኖ እንዲያድግ የሚያስችል ነዉ።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ እና የጥምረቱ አባላት መላው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ እንዲሁም የበረከት ስራ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ለ15 ቀናት የሚቆየዉ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር በአባይ ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል የቀጥታ ስርጭት ከምሽቱ 12 ሰአት እስከ ንጋቱ 12 ሰአት ነዉ የሚከናወነዉ።





Leave a Comment