#FastMereja | የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ከቦርድ ምርጫ ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤት በተላለፈ ዕግድ ምክንያት የፋይናንስ ችግር እንደገጠመውና ክለቡ ሊፈርስ ነው በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
በቅርቡ በተካሄደው የጠቅላላ ጉባኤ የምርጫ ውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ደጋፊዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዳቸው፣ ፍርድ ቤቱ አዲሱ ቦርድ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ዕግድ አስተላልፏል።
በዕግዱ ምክንያት ክለቡ አዲስ የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን መፈረምም ሆነ ሌሎች የገቢ ምንጮችን ማዘጋጀት ባለመቻሉ፣ የፋይናንስ ችግሩ ወደ ተወሳሰበ ደረጃ መሸጋገሩ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት ክለቡ በጽህፈት ቤት እና በስራ አስኪያጅ ደረጃ ብቻ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ችግሩን በውይይት ለመፍታት በደጋፊዎች የተጀመረው የሽምግልና መድረክ ላይ ክለቡ በቅን መንፈስ እየተሳተፈ መሆኑንና ለውይይት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
“ክለቡ ሊፈርስ ነው” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የተጋነነ ትንተና የሚሰጡ እና በክለቡ አመራሮችና ተጫዋቾች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚያካሂዱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ክለቡ አሳስቧል። በእነዚህ አካላት ላይ መረጃ የማሰባሰብና የህግ ሂደት የመጀመር ስራ መጀመሩንም ገልጿል።
ክለቡ ለማንም አካል ቴሌቶን የመሰብሰብ እውቅና እንዳልሰጠ አስታውቆ፣ ደጋፊዎች ክለቡን መደገፍ የሚችሉት በክለቡ ህጋዊ የባንክ አካውንቶች እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 928 ብቻ መሆኑን አስገንዝቧል።
