#FastMereja I የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የኮልፌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በከፍተኛ የአፍላቶክሲን (Aflatoxin) መርዛማ ንጥረ ነገር የተጠቃ 90 ኩንታል በርበሬ ወደ ኅብረተሰቡ ሳይሰራጭ ማስወገዱን አስታወቀ።
ምርቱ ከማህበረሰቡ በተገኘ ጥቆማ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 በሚገኘው የኮልፌ ሁለገብ የገበያ ማዕከል መደብር ውስጥ መገኘቱ ተገልጿል።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ሙኒራ ነጋሽ እንደገለጹት ለምግብነት ተዘጋጅቶ ሊሰራጭ የነበረው ይህ የበርበሬ ምርት ግምታዊ ዋጋው ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።
ምርቱ በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በላብራቶሪ ተፈትሾ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት እንዳለበት የተረጋገጠ ሲሆን ይህም ወደ ኅብረተሰቡ ቢሰራጭ ኖሮ ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች የሚያደርስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለሥልጣኑ ኅብረተሰቡ የሚገዛቸውን ለምግብነት የሚውሉ ማናቸውንም ምርቶች ጥራትና ደኅንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑን በማረጋገጥ ጤናውን እንዲጠብቅ አሳስቧል።
በተጨማሪም መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራትን በጋራ ለመከላከል ማንኛውም ዜጋ በ8864 ነፃ የጥቆማ መስመር በመደወል መረጃ እንዲሰጥና ትብብሩን እንዲያጠናክር መልእክት ተላልፏል።
