banner

ለሦስት ግዙፍ ኩባንያዎች የማምረት ፈቃድ ተሰጠ

#FastMereja I የማዕድን ሚኒስቴር የምርመራ ፈቃዳቸውን አጠናቅቀው ወደ ምርት ለሚሸጋገሩ የወርቅ፣ የብረት እና የፖታሽ አምራች ኩባንያዎች የምርት ፈቃድ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በፖታሽ ልማት፣ ZYBDIM ስቲል ማኑፋክቸሪንግ በብረት ልማት እንዲሁም ቤሮ ማይኒንግ በወርቅ ልማት ዘርፍ ፈቃድ ያገኙ አልሚዎች ናቸው።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቶቿን በማልማት ለሀገር ዕድገት ማዋል የሚያስችል ትልቅ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ብረትን በሀገር ውስጥ ማምረት አለመቻሉ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዛሬው ስምምነትም ይህ ችግር እልባት የሚያገኝ ሲሆን፣ ለዚሁ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መቀነስ እንደሚያስችልም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ፈቃዱን ያገኘው የብረት አልሚ ኩባንያ ወደ ምርት ከገባ በኋላ፣ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብረት የማምረት አቅም ይኖረዋል።

በወርቅ ምርት የተሰጠው ፈቃድም የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚያስችል ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ፈቃዱን ያገኙት አልሚዎች በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ የፋብሪካ ግንባታቸውን አጠናቅቀው ወደ ማምረት እንደሚሸጋገሩ ተገልጿል።

የማዕድን ሚኒስቴር ዛሬ ፈቃድ የሰጣቸው ሦስቱ አልሚዎች የ4.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ መሆኑም ተጠቁሟል።





Leave a Comment