#FastMereja I የእስራኤል መንግሥት በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጥገኝነት ጠያቂዎችን ማሰር የጀመረ ሲሆን፣ ከፊታችን ሚያዝያ ወር ጀምሮ እስከ 8 ሺህ የሚደርሱትን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ማቀዱ ተሰማ።
የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስደተኞቹ እንዳይባረሩ ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ውሳኔውን መተግበር ጀምሯል። እንደ ሲቪል ማኅበራት መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉ ስደተኞች ያሉ ሲሆን ጅምላ ስደት ከመጪው ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ይጀምራል።
የእስራኤል መንግሥት ጥር 2016 ዓ.ም ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ፣ ለኢትዮጵያውያን የጥገኝነት ጠያቂዎች ሰጥቶት የነበረውን “የቡድን ጥበቃ” (Group Protection) አንስቷል። ይህም ውሳኔ ስደተኞቹ በሀገሪቱ የመቆየት ሕጋዊ መብት እንዲያጡ አድርጓቸዋል።
ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ለከፍተኛ ደህንነት ስጋት እና ለኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚጋለጡ ድርጅቶቹ እየገለጹ ነው። በተለይ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አስተማማኝ ባልሆነበት ወቅት ይህ እርምጃ መወሰዱ “ወደ ጦርነት ቀጠና መመለስ ነው” በሚል እየተተቸ ይገኛል።
የእስራኤል የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ስደተኞችን ለመመለስ አስተማማኝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል።
እስራኤል ቀደም ሲል ከኤርትራና ከሱዳን የመጡ ስደተኞችን ለመመለስ ተመሳሳይ ጥረት አድርጋ በከፍተኛ ተቃውሞና በፍርድ ቤት እገዳ መቆሙ ይታወሳል። አሁን ግን በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተወሰነው ውሳኔ በፍርድ ቤት በመጽናቱ ግዴታውን ወደ መፈጸም ተገብቷል።
