banner

የራዳር ፍጥነት ቁጥጥር 75% የሚሆነው አግባብ ባልሆነ ቦታና ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጠ

​#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር አጠቃቀም 75% የሚሆነው ትክክለኛ ባልሆኑ ስፍራዎችና አደጋ በሚያስከትል መልኩ በመደበቅ የሚከናወን መሆኑን አንጋፋው የትራፊክ ደህንነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ገለጹ።

​በአውቶ ሴፍቲ ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ማብራሪያ የሰጡት ኢንስፔክተሩ፣ በአሁኑ ወቅት በመንገድ ትራንስፖርት ሰራተኞች እየተከናወነ ያለው የራዳር ቁጥጥር ከደህንነት መርሆዎች የወጣ መሆኑን ተችተዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ራዳር መያዝ ያለበት አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ Black Spots ላይ እንጂ፣ አሽከርካሪዎችን ለማጥመድ ታስቦ በማይመቹና በመደበቂያ ቦታዎች መሆን የለበትም ብለዋል።

​”ቁጥጥሩ እየተከናወነ ያለው አደጋ በሚያስከትል መልኩ እና በመደበቅ መሆኑ ትክክል አይደለም” ያሉት ኢንስፔክተር አሰፋ፣ ይህ አሰራር አሽከርካሪዎች በድንገት ፍጥነት እንዲቀንሱ በማድረግ ለተጨማሪ የኋላ ግጭት አደጋ ሊዳርግ እንደሚችል አስገንዝበዋል። የራዳር ቁጥጥር ዋና ዓላማ አደጋን መከላከል እንጂ ገቢ መሰብሰብ መሆን እንደሌለበትም በመረጃቸው አመልክተዋል።

​ይህ የባለሙያው አስተያየት በከተማዋ አሽከርካሪዎች ዘንድ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የነበረውን ቅሬታ የሚያጠናክር ሲሆን፣ የትራፊክ ቁጥጥር ስርአቱ ግልጽነትና ሙያዊ መርህን የተከተለ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

​መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም.

Leave a Comment