#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የናፍጣ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን ተከትሎ፣ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ረጅም የተሽከርካሪዎች ሰልፍ መታየት ጀምሯል። እጥረቱ በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ጫና የፈጠረ ሲሆን፣ በክልል ከተሞች ነዳጅ በጥቁር ገበያ እስከ እጥፍ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑ ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሚገኙ አብዛኞቹ የነዳጅ ማደያዎች “ናፍጣ የለም” የሚሉ ምልክቶች የተሰቀሉ ሲሆን፣ ነዳጅ ይገኛል ተብሎ በሚታሰብባቸው ውስን ማደያዎች ደግሞ የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለቀናት የሚዘልቅ ሰልፍ ይዘው ይገኛሉ። ይህ መስተጓጎል በከተማዋ የውስጥ ትራንስፖርት ላይ የሰዎች መከማቸትና የታክሲ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞች ደግሞ ችግሩ ይበልጥ ስር የሰደደ መሆኑ ተዘግቧል። በብዙ አካባቢዎች በማደያዎች ነዳጅ ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ፣ አሽከርካሪዎች ለጥቁር ገበያ ተጋላጭ ሆነዋል። በተለይም በግብርና እና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት ከወትሮው የሊትር ዋጋ እጅግ የላቀ ክፍያ እየከፈሉ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህንን የነዳጅ እጥረት ሰበብ በማድረግ በክልል ከተሞች የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ። በመንግስት በኩል የኢራን ጦርነት የነዳጅ እጥረት ሊያስከትል ስለሚችል ቆጥቡ የሚል መልዕክት ሲተላለፍ ቢቆይም በተለይ የናፍጣ እጥረት ከጦርነቱ በፊት የተከሰተ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።
መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም.
