#FastMereja I በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ ስም “ዘመናዊ ታክሲዎችን በዱቤ እናቀርባለን” በሚሉ አማላይ ማስታወቂያዎች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ከዜጎች የሰበሰበው የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል ዮሐንስ ክስ ተመሰረተበት።
ተከሳሹ በማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀምና አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት በፈጸመው መጠነ ሰፊ ማጭበርበር በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ 19 ተደራራቢ ክሶች ቀርበውበታል።
የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ዝርዝር መሠረት፣ ግለሰቡ ወንጀሉን የፈጸመው በንግድና በሕጋዊ ሽፋን በተደራጀ “የነጭ ኮሌታ ሳይበር ማጭበርበር” ስልት መሆኑ ተመልክቷል።
ተከሳሹ በ2013 ዓ.ም “ሄሎ ታክሲ” እና “ሄሎ መኪና” የተባሉ ድርጅቶችን በማቋቋም፣ የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት ዘመናዊ መኪናዎችን በዱቤ እንደሚያቀርብ በማብሰር ከ5 ሺህ በላይ ዜጎችን መዝግቧል። ለእያንዳንዱ ምዝገባና ቅድመ ክፍያ እስከ 247,500 ብር ካሰባሰበ በኋላ ድርጅቱን ዘግቶ መሰወሩ ተገልጿል።
ዳንኤል ዮሐንስ ቀደም ሲል በዓለም ዋንጫ ስም ማጭበርበር ፈጽሞ በኢንተርፖል ከተያዘው ግርማይ ገብረሚካኤል (አስካል) ከተባለ ግብረ-አበሩ ጋር በመሆን፣ በ2016 ዓ.ም “ፊንቴክ ኢንቨስትመንት” የተባለ ድርጅት በ7 ሚሊዮን ብር ካፒታል አቋቁሟል።
ድርጅቱ የቻይናውን “ቢዋይዲ” (BYD) የኤሌክትሪክ መኪኖች በዱቤ እንደሚያቀርብ በማስመሰል፣ ታዋቂ አርቲስቶችንና ቲክቶከሮችን በመጠቀም ሰፊ ማስታወቂያ አስነግሯል። በመስቀል አደባባይና በስካይ ላይት ሆቴል መኪናዎችን እንዳስረከቡ የሚያሳዩ የሐሰት ምስሎችን በማሰራጨት የሕዝብን እምነት ማግኘታቸው ተረጋግጧል።
ተከሳሹ ከ1,430 በላይ ግለሰቦችን በመመዝገብ ከእያንዳንዱ ሰው ከ950 ሺህ እስከ 1.86 ሚሊዮን ብር የሰበሰበ ቢሆንም፣ ለጥቂት የጥቅም ተጋሪዎቹ ብቻ መኪና በመስጠት የተቀሩትን ሳይበድል ቀርቷል። በማስታወቂያው ላይ ግን 520 መኪናዎችን እንዳከፋፈለ በመግለጽ የሐሰት ሪፖርት ሲያቀርብ እንደነበር ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።
ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ እና የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅን በመተላለፍ ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል።
መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም


