banner

ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ህፃናት ለመደገፍ የታለመው የ9 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ተከናወነ!

#Fastmereja I ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት ማህበር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናትን እና እናቶቻቸውን ለመደገፍ እንዲሁም ግንዛቤ ለመፍጠር ያዘጋጀው “በነሱ ጫማ” የተሰኘ የ9 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ በዛሬዉ እለት በደመቀ መልኩ ተከናዉኗል።

በዕለቱ በተካሄደው መርሃ-ግብር ላይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የጉዞው ዋነኛ ዓላማ ”ጊፍትድ ኽርትስ” (Gifted Hearts) የተሰኘውንና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚሰጠውን ባለ 6 ወለል ህንፃ ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚውል ገቢ ማሰባሰብ መሆኑ ተገልጿል።

የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር አሳየች ይርጋ በዝግጅቱ ላይ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለ164 ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናትና ለ164 እናቶች መጠለያ፣ የምገባ፣ የህክምና እና የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ነዉ የገለፁት።

“ይህ ጉዞ ህፃናቱና እናቶቻቸው በየቀኑ የሚጓዙበትን አስቸጋሪ መንገድ ለህብረተሰቡ በተግባር ለማሳየት ‘በነሱ ጫማ’ ተብሎ የተሰየመ መሆኑን አያይዘዉ ገልፀዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ ማጠናቀቂያ 146 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ በዕለቱ በተሸጡ ቲሸርቶችና በተደረጉ ድጋፎች ገቢ መገኘቱ የተገለፀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የህንፃው የምድር ስር (Basement) ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪው ስራ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

ትኩረት ለሴቶችና ለሕፃናት ማኅበር ላለፉት 19 ዓመታት በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ የተሰማራ አንጋፋ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ የአእምሮና የአካል እድገት ውስንነት ያለባቸው ህፃናትና እናቶቻቸው ላይ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡





Leave a Comment