#Fastmereja:አዲስ አበባ የነገዎቹን የእግር ኳስ ኮከቦች በማፍራት ላይ የሚገኘው የአሸናፊ ግርማ እግር ኳስ አካዳሚ፣ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ጉልህ አሻራ ላሳረፉ አንጋፋ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች እና ጋዜጠኞች በካፒታል ሆቴል ደማቅ የእውቅና እና የሸልማት መርሃ-ግብር አከናወነ።
አካዳሚው በየዓመቱ ለማከናወን ካቀደው የክብር መርሃ-ግብር መካከል የዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር ስነ-ስርዓት የተከናወነ ሲሆን፣ ዓላማውም ታዳጊዎችን ከመቅረጽ ባለፈ ለሀገር ስፖርት እድገት የደከሙ ባለሙያዎችን ማበረታታትና ምስጋና ማቅረብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዕለቱ በልዩ ሁኔታ እውቅና ከተሰጣቸው መካከል አንጋፋዎቹ ስፖርተኞች በቀለ እልሁ፣ አወቀ አሰፋ እና አንዷለም ንጉሴ (አቤጋ) የገንዘብ እና የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በተለይም የቀድሞው ኮከብ አንዷለም ንጉሴ (አቤጋ) ከአካዳሚው ሽልማት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት በዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በኩል ድንገተኛ (Surprise) የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ እዉቅና እንዲሁም ሽልማት የተበረከተላቸዉ ተጫዋቾች፦ፍስሀ በጋሻው፣ ብርሃኑ ፈዬራ፣ አንዋር ያሲን፣ አንዋር ሲራጅ፣ ካሊድ መሀመድ፣ አዳነ ግርማ፣ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ፍቅሩ ተፈራ እና ረውዳ ዓሊ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በአሰልጣኝነት ዘርፍ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ኢንስትራክተርአብርሃም መብርሃቱ፣ እንዲሁም የወርልድ ስፖርት ጋዜጣ መስራች ጋዜጠኛ ጥሩነህ ካሳ ተሸልመዋል፡፡
የአካዳሚው መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አሸናፊ ግርማ፣ ይህ መርሃ-ግብር በቀጣይ አመታት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፆ በቀጣይ አሁን ላይ ያልተካተቱትን ኮከብ የስፖርት ቤተሰቦችን በማካተት ሽልማቱንም በማሳደግ እንደሚሰራ ገልጿል።
የአካዳሚውን ጥረት ያደነቁት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ አካዳሚው በቅርቡ ለሚያዘጋጀው ዝግጅት የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል የገቡ ሲሆን ለአንዳንድ ተጫዋቶች የገንዘብ ሽልማት እንደሚያበረክቱ በመድረኩ ቃል ገብተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ እንደ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ያሉ ታዋቂ የስፖርት ሰዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ይህ መድረክ አሸናፊ ግርማ “የታላላቆቹ ታናሽ” በመሆን ለዘርፉ ያሳየው ትልቅ አክብሮትና ለሌሎች ተቋማትም አርአያ የሚሆን ተግባር ተብሎ ተሞግሷል።




