banner

በአዲስ አበባ ከ122 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች እና 37 ሺህ እግረኞች በህግ ተጠየቁ

​#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዘጠኝ የበጀት ወራት በተከናወነ የትራፊክ ቁጥጥር፣ በከባድ የደንብ መተላለፍ ጥፋት የተገኙ 122 ሺህ 957 አሽከርካሪዎች እና ከ37 ሺህ በላይ እግረኞች ላይ አስተዳደራዊ እና የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታወቀ።

​ባለስልጣኑ በከተማዋ በሚገኙ 40 ዋና ዋና መንገዶች ላይ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል፣ የቅጣት እርምጃ ከተወሰደባቸው አሽከርካሪዎች መካከል 80 ሺህ የሚሆኑት ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከርከሩ የተገኙ ናቸው። በተጨማሪም 1 ሺህ 653 አሽከርካሪዎች ከአልኮል መጠን በላይ ጠጥተው በማሽከርከር፣ 7 ሺህ 26ቱ ደግሞ ስልክ እያነጋገሩ ሲያሽከርከሩ በመገኘታቸው የእርምት እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

​የደህንነት ጥንቃቄን በተመለከተ 3 ሺህ 66 አሽከርካሪዎች የደህንነት ቀበቶ ባለማሰራታቸው፣ እንዲሁም 585 የሞተር ብስክሌተኞች የጭንቅላት መከላከያ (ሄልሜት) ባለማድረጋቸው ተቀጥተዋል። በሌላ በኩል፣ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ እንቅፋት የፈጠሩ 743 ተሽከርካሪዎች በክሬን እንዲነሱ መደረጉን ተቋሙ ገልጿል።

​በእግረኞች ላይ የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ፣ በአጠቃላይ 37 ሺህ 853 እግረኞች በደንብ መተላለፍ ተጠያቂ ሆነዋል። ከነዚህም መካከል 21 ሺህ 202 የሚሆኑት የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 16 ሺህ 651 እግረኞች ደግሞ የገንዘብ ቅጣቱን በከፊልም ሆነ በሙሉ በመተካት የማህበራዊ አገልግሎት ስራ እንዲሰሩ ተደርጓል።

​በተያያዘ ዜና፣ በመስቀለኛ መንገዶች እና በአደባባዮች ላይ ግብይት የፈጸሙ እንዲሁም ምጽዋት የሰጡ 4 ሺህ 500 ግለሰቦችም በደንብ መተላለፍ መቀጣታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል።

​መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም Via ኢትዮ ኤፍ ኤም

Leave a Comment