#FastMereja I በወላይታ ዞን በዴሳ ከተማ ትናንት ምሽት በደረሰ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ በስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ አስታውቋል።
አደጋው ትናንት ምሽት 1:00 ሰዓት አካባቢ የተከሰተ ሲሆን፣ ከሶዶ ወደ ሐዋሳ ይጓዝ የነበረ አንድ ተሳቢ የጭነት ተሽከርካሪ በዴሳ ከተማ ውስጥ መስመሩን ስቶ በከፍተኛ ፍጥነት በመጓዝ መንገድ ዳር የነበሩ ሞተር ሳይክልና ባጃጅን ገጭቷል። ተሽከርካሪው በዚሁ ሳይገታ መንገድ ጥሶ በመውጣት ሦስት የመኖሪያ ቤቶችን ደርምሶ መግባቱ ታውቋል።
በአደጋው ሳቢያ የባጃጅ አሽከርካሪው ወዲያውኑ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ ተሽከርካሪው በደረመሳቸው ቤቶች ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ለማዳን የተደረገው ጥረት እጅግ ፈታኝ እንደነበር ተገልጿል። እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት፦
የሟቾች ቁጥር የአሽከርካሪውን ጨምሮ 7 ደርሷል። በ4 ሰዎች ላይ ከባድ፣ በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሷል።ሦስት መኖሪያ ቤቶች እና ሁለት ተሽከርካሪዎች (ባጃጅና ሞተር ሳይክል) ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የአደጋውን መንስኤ እና በንብረት ላይ የደረሰውን ዝርዝር የውድመት መጠን በማጣራት ላይ ይገኛል። አደጋው የደረሰበት አካባቢ በተደጋጋሚ መሰል ክስተቶች የሚስተዋሉበት በመሆኑ፣ አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የዞኑ ፖሊስ አሳስቧል።
ሚያዝያ 02 ቀን 2018 ዓ.ም
