banner

ከ6.3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

​#FastMereja I በ2018 የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ተብለው ከታቀዱ ተማሪዎች መካከል 6.3 ሚሊዮን የሚሆኑት አለመመዝገባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ገለጸ። ለተማሪዎቹ ምዝገባ መታደቅ ዋና ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው በሀገሪቱ የሚገኙ ከ2,600 በላይ ትምህርት ቤቶች ስራ አለመጀመራቸው ነው።

​ትምህርት ሚኒስቴር ለፓርላማው የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በላከው ባለ 108 ገጽ ሪፖርት፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 33.5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ እንደነበር አስፍሯል። ሆኖም ከተያዘው እቅድ ውስጥ 19 በመቶ ያህሉን ወይም 6,380,932 ተማሪዎችን መመዝገብ እንዳልተቻለ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

​ለተማሪዎቹ ምዝገባ አለመሳካት በዋናነት የተጠቀሰው በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙትን ጨምሮ በአጠቃላይ 2,672 ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸው ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትምህርት ቤቶቹ ስራ ያልጀመሩት በ“ሰው ሰራሽ” እና “ተፈጥሮአዊ” ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ቢገልጽም፣ ስለ ችግሮቹ ዝርዝር ሁኔታ ግን በሪፖርቱ ላይ አላብራራም።

ዘገባው የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው

Leave a Comment