#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ተመርቋል። የከተማዋን የኢኮኖሚ መዋቅር ያዘምናል የተባለውና ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው ይህ ግዙፍ ፓርክ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይፋ እንዳደረጉት፣ ፓርኩ በ93.9 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን 116 የማምረቻ ቦታዎችን፣ 356 ቢሮዎችን እና 248 ሱቆችን በውስጡ ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ጊዜ ከ400 በላይ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ስፍራ፣ የ4 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣ 25 የሰዎችና ዕቃዎች ማጓጓዣ ሊፍቶች እንዲሁም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት የሚሰጡ 10 ትራንስፎርመሮችና ዘመናዊ ጀነሬተሮች ተገጥመውለታል።
ይህ ሁለገብ የኢንዱስትሪ መንደር ከማምረቻ ዘርፉ ባሻገር ሆቴል፣ ካፌቴሪያ፣ የጥራት ቁጥጥር ማዕከል፣ ራሱን የቻለ የውኃ ጉድጓድ እና ዘመናዊ የቆሻሻ ማጣሪያ ሥርዓት ተሟልቶለታል። በተጨማሪም የሕፃናት ማቆያ፣ የስፖርት ሜዳዎችና ሰፊ የአረንጓዴ ስፍራዎች እንደተካተቱበት ተገልጿል። ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ፣ ጥራትና በጀት መጠናቀቁን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ለግንባታው ስኬት ሌት ተቀን ለደከሙ የሥራ ተቋራጮች፣ አመራሮችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምስጋና አቅርበዋል።




