banner

“የቡና ስኮላርሺፕ” ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የአውሮፓን የትምህርት በር ከፈተ

#FastMereja I “የቡና ስኮላርሺፕ” ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡና በላቀ ውጤታቸው ለተመረጡ ተማሪዎች ወደ አውሮፓ አቅንተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል ወሳኝ የገንዘብና የማማከር ድጋፍ በአዲስ አበባ አበረከተ።

በስዊድንና በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተመሰረተው ይህ ተቋም፣ በከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ያለፉ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

የጃታኒ አሊ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሚሊቻ ሎጄ በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ባህል የማገናኘትና የአንድነት ተምሳሌት የሆነውን “ቡና” የሚለውን ስያሜ የያዘው ተማሪዎችን ከዓለም አቀፍ ዕድሎች ጋር ለማስተሳሰር በማለም ነው። የስራ ፈጣሪው አቶ ቢኒያም ፍቃዱ ራዕይም ተሰጥኦ በገንዘብ እጥረት እንዳይታፈን በማድረግ በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎችና የንግድ ማህበረሰቡ የዚህ ታሪካዊ ንቅናቄ አካል እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረብ ነው።

ተቋሙ ወደፊትም በመላው ዓለም ከሚገኙ ከ800 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያለውን ትስስር በማስፋት በጤና፣ በግብርና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ለውጥ የሚያመጡ ምሁራንን የማፍራት ሰፊ እቅድ እንዳለው አስታውቋል።





Leave a Comment