banner

ምርጫ ሰላም እንዲሰፍን ከ1 ሺሕ በላይ ዜጎች የሚሳተፉበት አገር አቀፍ የጋራ ጸሎት ሊደረግ ነው

​#FastMereja I የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መጪውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ፣ ከ1 ሺሕ በላይ ዜጎችና የሰባት የሃይማኖት ተቋማት አባቶች የሚሳተፉበት ታላቅ የጋራ የጸሎት እና የዱአ መርሃግብር ማዘጋጀቱን በይፋ አስታወቀ።

​ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የአደባባይ የጸሎት ስነ-ስርዓት በቀጣዩ እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ በአራዳ ፓርክ በድምቀት እንደሚከናወን ተገልጿል። የአደባባይ ጸሎቱ ዋና ዓላማ መጪው አገራዊ ምርጫ ሁከትና ግጭት ተወግዶለት በሰላማዊ ድባብ እንዲጠናቀቅ ለመማጸን መሆኑን የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደሰ አስታውቀዋል። ከዋናው ማዕከል በተጨማሪ በተመሳሳይ ሰዓት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በየአካባቢያቸው በጋራ ጸሎት እንደሚያደርጉ ተረጋግጧል።

​የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሰል አገራዊ አጀንዳዎች እና የጋራ ስጋቶች ሲደቀኑ ምዕመናንን ያስተባበረ የጋራ ጸሎት ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም። ቀደም ሲል የኮቪድ-19 ወረርሺኝ አገርን በፈተነበት ወቅት ተመሳሳይ የአደባባይ የጸሎት መርሃግብር በማዘጋጀት ህዝቡን ለፈጣሪው እንዲጮህ ማድረጉ ይታወሳል። ጉባኤው አገራዊ አንድነትን ለመጠበቅና ሰላምን ለማስፈን መሰል የጋራ የጸሎት መርሐግብሮችን በተከታታይ ማድረጉን እንደሚቀጥልበትም ጠቅላይ ጸሐፊው አክለው ገልጸዋል ሲል ሀገሬ ቲቪ ነው የዘገበው።

Leave a Comment