banner

ራስን የማጥፋት ድርጊትንና የሱስ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ ይፋ ሆነ!

#Fastmereja በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተለይም በወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ እየተስፋፋ የመጣውን ራስን የማጥፋት (Suicide) ድርጊት እና የሱስ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ ይፋ ሆነ።

ንቅናቄው “በሞቴ – ከመሞት መሰንበት” በሚል መሪ ቃል ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት በቀጣይ ሦስት ወራት ማህበረሰቡን የማንቃት እና የተለያዩ ስራዎች የሚሰሩበት እንደሆነ ተገልጿል።

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይና የቺፍ ኦፍ ስታፍ አቶ አሳልፈው አማካኝነት በይፋ በተበሰረው በዚህ ንቅናቄ ላይ እንደተመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት የሚጥሩት የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስቶች (Psychiatrists) ቁጥር ከ120 በታች መሆኑ የባለሙያ እጥረቱን አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል።

አቶ አሳልፈዉ አክለዉም ይህንን ክፍተት ለመሙላትም እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን ከባለሙያዎች ጋር በቀላሉ ለማገናኘት የሚያስችል የዕገዛ መስመር እና የመረጃ ቋት (Database) የማደራጀት ሥራ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በመድረኩ ላይ እንደተብራራው፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች (በተለይም በቴሌግራም ግሩፖች) አማካኝነት የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች (Cyberbullying) እና የእኩዮች ጫና ለችግሩ መባባስና ለተማሪዎች ሕይወት ማለፍ ዋነኛ መንስኤ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ።

ይህንን ለመመከት በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአእምሮ ጤና ድጋፍ የሚሰጡ 300 የሚጠጉ ተማሪ አምባሳደሮች የተሰማሩ ሲሆን፣ በቀጣይም ከታዋቂ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች (Influencers) ጋር በመተባበር ሰፊ የብዙኃን መገናኛ ዘመቻ የሚካሄድ ይሆናል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የ “QPR” (ጠይቅ፣ አሳምን እና መምሪያ ስጥ) የራስን ሕይወት ማጥፋት መከላከያ ሥልጠና ለትምህርት ቤቶችና ለሃይማኖት ተቋማት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ከመድኃኒትና ከሱስ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ፤ የፀረ-ጭንቀትና እንደ ትራማዶል (Tramadol) ያሉ ማስታገሻ መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ለሕፃናት እንዳይሸጡ ፋርማሲስቶችን የቁርጠኝነት ፎርም የማስፈረም እና የኮንትሮባንድ ሰንሰለቶችን የመበጠስ ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም በልደታ ክፍለ ከተማ የሙከራ (Pilot) ፕሮጀክት ጣልቃ ገብነት በቅርቡ እንደሚጀምር ነዉ የተገለፀዉ።

በሌላ በኩል፤ ከ40 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው የሕብረተሰብ ክፍል ለተለያዩ ሱሶች ተጋላጭ በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ 42 ማኅበራትን አቅፎ እስካሁን ከ21 ሺህ በላይ ዜጎችን በግንዛቤና በሕክምና ድጋፍ የረዳው የ«አይሰለጥንብኝም!» ንቅናቄ ማኅበረሰቡን የማንቃትና የማሕበራዊ ሚዲያ ስትራቴጂዎችን የመተግበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚህ ሀገራዊ ንቅናቄ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋገጠ ሲሆን፣ አሁን የተጀመረው ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በስፋት እንዲወርድና እንዲዋቀር፣እንዲሁም ሥራውን በዘላቂነት ለማገዝ የገቢ ማሰባሰብ (Fundraising) እንደሚከናወን አቅጣጫ ተቀምጧል።





Leave a Comment