banner

ሀገሬ ቴሌቪዥን የ2026 ዓለም ዋንጫን እና ኦሊምፒክን በቀጥታ የማስተላለፍ ታሪካዊ መብት አገኘ!

​#FastMereja I በኢትዮጵያ የግል ቴሌቪዥን ስርጭት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ተጻፈ! የሀገሪቱ ስፖርት እውነተኛ ድምጽ ሆኖ ብቅ ያለው ሀገሬ ቴሌቪዥን፣ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶችን በይፋ የማቅረብ ሙሉ መብት ካለው ማርኬቲንግ እና ሚዲያ ሶሉሽን (MMS) ጋር የረጅም ጊዜ ስርጭትን ያካተተ ታሪካዊ የአራት ዓመት ውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

​ይህ ስምምነት በሀገሪቱ የግል ሚዲያ ታሪክ የመጀመሪያው ሲሆን፣ መላው የሀገራችን የስፖርት አፍቃሪዎች በጉጉት የሚጠብቋቸውን ውድድሮች በከፍተኛ ጥራትና በሰፊው በቀጥታ ለመመልከት ያስችላቸዋል።

​በዛሬው ዕለት በተፈረመው ውል መሰረት ሀገሬ ቴሌቪዥን የሚከተሉትን ታላላቅ ውድድሮች በብቸኝነት ያቀርባል። የሀገራችን የዘላለም ኩራት የሆኑት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በሙሉ የማስተላለፍ ብቸኛ መብት፣ ​የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደምቀው የሚነግሱበት እና የዓለም ምርጥ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት የኦሊምፒክ ውድድር በሙሉ አቅምና በጥራት፣ የ2026 የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ (FIFA World Cup 2026) አስደናቂ ፍልሚያዎችን በግል ሚዲያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በብቸኝነት እና በነጻ ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ልዩ የስርጭት መብት አግኝቷል።
​
​ሀገሬ ቴሌቪዥን ታላላቅ ስፖርታዊ ሁነቶችን በቀጥታ ከማስተላለፍ ባሻገር፣ ተመልካቾቹን ይበልጥ ለማርካት ሰፊ ዝግጅት አድርጓል የተባለ ሲሆን ​በሌሎች አዳዲስ የስፖርት እና መዝናኛ ይዘቶች፣ እንዲሁም ባህላዊና ሁለንተናዊ ሥራዎች ላይ በሰፊው በመሰማራት አዳዲስ ጉዳዮችን ይዞ እንደቀረበ ተገልጿል። !





Leave a Comment