#FastMereja I የወሎ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወህዴፓ) 7ኛውን ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ መጠናቀቅ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ፓርቲው በመግለጫው ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን የገለጸ ሲሆን፣ በሂደቱ ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖችንና ያጋጠሙ ጉድለቶችን በዝርዝር አመልክቷል።
በዚህ የምርጫ ሂደት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለውን የኦንላይን ዕጩ ምዝገባ ሥርዓት በመጠቀም ፓርቲው በ214 የክልልና የከተማ አስተዳደር ምርጫ ክልሎች ዕጩዎቹን ማቅረብ እንደቻለ አስታውቋል። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ቦርዱ ያመቻቸውን ነፃ የሚዲያ የአየር ሰዓትና የክርክር መድረክ በመጠቀም ፕሮግራሙን ለሕዝብ ማድረሱን ገልጿል። ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው የድምፅ መስጠት ሂደት ሕዝቡ ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ በመውጣት ድምፅ በመስጠቱ ፓርቲው ምስጋናውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን በዕቅድና በፕሮግራም ለመምራት ያደረገውን ጥረት ያደነቀው ወህዴፓ፣ በምርጫው ዕለት ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ክፍተቶች መታየታቸውንና እነዚህም ክፍተቶች በራሱ በቦርዱ ተለይተው ለቀጣይ ሥራዎች መሻሻያ እንዲሆኑ ጠይቋል። የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትና የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ምርጫው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጾም በሪፖርቱ አጉልቷል።
በተያያዥም፣ ምርጫውን ለማደናቀፍ፣ የሃይማኖትና የብሔር ግጭት ለመፍጠር እንዲሁም በንጹኃን ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሴራ በሕዝቡና በፀጥታ ኃይሉ ቅንጅት ሊከሽፍ እንደቻለ በመግለጫው ተጠቅሷል። ፓርቲው በመጨረሻም የሕዝብ ድምፅ ተከብሮ የምርጫው ውጤት ይፋ እስከሚሆን ድረስ ሂደቱን በትዕግሥት እንደሚጠባበቅ አስታውቋል።




